"ለኢትዮጵያ ደማችንን ሰጥተን ለፍቅር፣ይቅርታና እድገት የማንሳሳ መሆኑን እናሳያለን" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

54
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 "ለኢትዮጵያ ደማችንን ሰጥተን ለፍቅር፣ይቅርታና እድገት የማንሳሳ መሆኑን እናሳያለን" ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በመስቀል አደባባይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች አጋርነታቸውን ለማሳየት ዛሬ ደም ለግሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ "በቅዳሜ ቀን የፍቅርና የይቅርታ ቀን አውጀን ወንድምና እህቶቻችን ደማቸው ፈሷል፤ ለእነርሱ ደም መለገስ ያስፈልጋል" ብለዋል። "ኢትዮጵያ የተራበችው ፍቅር" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ "ፍቅር የተራበውን ህዝባችንን ፍቅር ለመመገብና እኛም ፍቅር ለመቀበል የነበረን ጥረት ፍቅር በማይወዱ ኃይሎች በከንቱ ወንድምና እህቶቻችን ደማቸው ፈሷል" ብለዋል። ያንን የፈሰሰ ደም ለመተካት ደግሞ "በዕለቱ ምንም ጉዳት ያልደረሰብን ጤነኛ ሰዎች ደም በመለገሰ ፍቅራችንን ልናረጋግጥ ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል። ፍቅር በመስጠትና ፍቅር በመቀበል በይቅርታ የኢትዮጵያን መፃዒ ጉዞ ማሳመር እንደሚቻል ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፍቅር ውጪ ያለ ሁሉም መንገድ ከንቱ በመሆኑ "ለኢትዮጵያ ደማችንን ሰተን ለፍቅር ለይቅርታ ለእድገት የማንሳሳ መሆኑን እናሳያለን" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ህብረተሰቡ ለተጎዱ ወገኖች ደም በመለገስ ያለውን ፍቅር እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ የጤና ጥበቃው ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ደም የሰጡ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ትናንት የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችም ደም መለገሳቸው ይታወሳል። በተያያዘ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ደጉ አንዳርጋቸውም በህክምና ላይ የሚገኙትን ተጎጂዎች በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቃቱ በኋላ የተለያዩ ሰዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ደም ለጋሾች እና በጎ ፈቃደኞች ላሳዩት ትክክለኛ አጋርነትም ትናንት አመስግነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ለተጎጂዎች ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተደረገ ያለውንም ጥረት አድንቀዋል። በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለተጎጂዎች እርዳታ የሚውል የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት ወራት ላከናወኑት ተግባር እውቅና እና ምሰጋና ለማቅረብ በተደረገው ሰልፍ ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 150 በላይ የሚሆኑ ለከባድና ቀላል ጉዳት ተዳርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም