በትግራይ ምእራባዊ ዞን በግብር አከፋፋል ዙሪያ ይታዩ ነበሩ ችግሮች እየተቃለሉ መጥተዋል --- ነጋዴዎች

66
ሁመራ ኢዜአ ጥር 18/2012  በትግራይ ምእራባዊ ዞን በግብር አከፋፈል ላይ ይታዩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግዴታውን በአግባቡ ለመወጣት እንዳስቻለው የንግድ ማህበረሰብ አባላት ገለፁ ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከገለጹት የንግድ ማህበረሰብ አባላት መካከል በሁመራ ከተማ በብረታ ብረት ስራ የተሰማሩ አቶ ፍሳሃ አረጋዊ እንዳሉት ከአሁን በፊት የነበረው የግብር ትመና ፍትሃዊነት የጎደለውና የገቢ አቅምን ያላገናዘበ ነበር ብለዋል። በዘርፉ ይታዩ የነበሩት ችግሮች ከአንድ አመት ወዲህ እየተቀረፉ በመምጣታቸው አሁን የተጣለባቸውን ግብር ወቅቱን ጠብቀው እየከፈሉ ከመሆናቸው በላይ በሚከፍሉት ገቢ እንደማይከፉም ተናግረዋል። በበጀት አመቱ የተጣለበቸውን 14ሺህ ብር ግብር ቅድሚያ መክፈላቸውንና አሁንም ፍትሀዊና የሚመጥናቸው ግብር ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከሁለት አመት በፊት ፍትሃዊነት በጎደለው የግብር ትመና 250ሺህ ብር እንዲከፉሉ መጠየቃቸውን የተናገሩት ደግሞ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የትርካን ቀበሌ ነዋሪና የሰሊጥ ነጋዴ አቶ አለምብርሀን ተክለሀይማኖት ናቸው፡፡ የተጣለባቸውን ግብር ፍትሀዊነት የጎደለው በመሆኑ እንዲሻሻልላቸው እስከ ክልል ደረጃ ቅሬታ ለማቅረብ ተገድደው እንደነበር አስረድተዋል። በግብር ትመና ላይ ችግር መኖሩን ከመንግስት ጋር መግባባት ላይ በመደረሱ  በያዝነው አመት 30 ሺህ ብር መክፈላቸውን አስረድተዋል። በፀገዴ ወረዳ ዳንሻ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ የተሰማሩ ወይዘሮ ሀገረ ገብሩ በበኩላቸው ከሁለት አመት በፊት በግብር አከፋፈል ላይ አብዛኛው ማህበረስብ ቅሬታ ያስነሳ እንደነበር ገልጸዋል። ባለፈው ሀምሌ ወር 7 ሺህ ብር መክፈላቸውን ጠቅሰው ይህም አቅማቸው ያገናዘበና ተገቢ ክፍያ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሚከፍሉት ግብር ተመልሶ ለልማት እየዋለ በመሆኑ በቀጣይም በወቅቱ ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዞኑ ገቢዎች ለልማት የጽህፈትቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሚዛን ታደሰ በበኩላቸው በዞኑ ከ35 ሺህ በላይ በንግድ የተሰማራ ማህበረሰብ መኖሩን ገልጸዋል። በጥናት ላይ  የተመሰረተ ሳይንሳዊ አሰራር ባለመኖሩ አንዳአንድ የንግድ ማህበረሰብ አባላት  ከመጠን በላይ ግብር ለመክፈል ይገደዱ እንደነበር አምነዋል። አሁን በንግድ ጥናቱ ላይ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በማካተት የሚካሄድ በመሆኑ ይነሱ ከነበሩ ቅሬታዎች መካከል አብዛኛውን መፍታት እንደተቻለ አስረድተዋል ። በመንግስት ላይ ይታዩ የነበሩት ችግሮች እየተቃለሉ ቢመጡም በንግድ ማህበረሰብ በኩል ግን ግብር መሰወርና ለሸጡት እቃና ለሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ ያለመስጠት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ ብለዋል ። ይህን ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ሶስት ነጋዴዎች እያንዳአንዳቸው 50 ሺህ ብር እንዲቀጡ 32 ነጋዴዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው መደረጉን ገልፀዋል ። በበጀት አመቱ በዞኑ ከግብር 338 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት 150 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ አስረድተዋል ። የዘንድሮው የ6 ወር ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ56 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው ተብሏል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም