ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በ560 ሚሊዮን ብር የመምህራን መኖሪያ ቤቶች እያስገነባ ነው

87
ሶዶ ጥር 16/2012 ኢዜአ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች እያስገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተክሌ ሌዛ እንደገለፁት የመኖሪያ ቤት ችግር መምህራን ተረጋግተው ስራቸውን እንዳይሰሩ እንቅፋት በመሆኑ የመምህራን ፍልሰትን ለማስቆም ታስቦ ግንባታው መጀመሩን ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ፍልሰቱን ለማስቆም፣ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ሳይስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ ማድረግ ያስችላል ። ከ200 ለሚበልጡ መምህራን የመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚሰጡ አራት ህንጻዎች ግንባታቸው በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤቶቹ ኢንተርኔትን ጨምሮ የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው እንደሆነም ጠቁመዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው መምህራን ከየትኛውም ተጽዕኖና ጫና ነጻ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ግንባታው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ። ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ ካለው ግንባታ በተጓዳኝ ከመንግስትና ከግል ባንኮች ጋር በመቀናጀት የመምህራኑን የመኖሪያ ቤት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል። በሃገራችን መምህራንና ተመራማሪዎች በስራቸው ላይ ብቻ በማተኮር ሲለፉ ቆይተው በስተመጨረሻ መወደቂያ አጥተው በኪራይ ቤት ሲንከራተቱ ማየት የተለመደ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ታከለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህን ችግር ለመፍተት የተደራጀ መፍትሄ መፈለግ አለባቸው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት እያገለገሉ ያሉት አቶ እዮብ አጫ በሰጡት አስተያየት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከ15 ዓመት በላይ ማገልገላቸውን ገልጸው የመኖሪያ ቤት ስለሌላቸው ተረጋግተው ለመስራት እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እያከናወነ ያለው ተግባር በሙያቸው ተረጋግተው በትኩረት እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማርና የምርምር ሥራውን እያከናወኑ የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ መምህራን እንዳሉት መረጃዎች ያመላክታሉ ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም