ዛሬ በተደረገ ተስተካካይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት አርባ ምንጭ ከተማን ሁለት ለአንድ አሸነፈ

80
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት አርባምንጭ ከተማን ሁለት ለአንድ አሸነፈ። በአዲስ አባባ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአርባ ምንጭ ከተማው ተመስገን ካስትሮ በደደቢቱ አጥቂ አቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ከመረብ በማሳረፍ መሪ ማድረግ ችሏል። ጌታነህ ያስቆጠራት ግብ በዘንድሮው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 12 ከፍ አድርጎለታል። ስዩም ተስፋዬ ከአስራ ስድስት ከሃምሳ ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ሁለት ቋሚ በመግጨት  ሁለተኛውን ግብ ለደደቢት አስቆጥሯለ። ግቡም አስደናቂ ሊባል የሚችል ነው። ከእረፍት መልስ አርባ ምንጭ ከተማ በተመስገን ካስተሮ ግብ ሁለት ለአንድ መሆን ቢችልም ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። በጨዋታው ላይ የደደቢቱ ስዩም ተስፋዬ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በተጨማሪም ጋናውያን  የደደቢት ተጫዋቾች ከድር ኩሊቫሊና አማራህ ክሌይመንት ቢጫ ካርድ ሲመለከቱ ከአርባ ምንጭ ከተማ በኩል አለልኝ አዘነም ቢጫ ካርድ መመልከት ችሏል። በጨዋታው ላይ የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የአሰልጣኝ አባላት ያልተገባ ውሳኔ ተሰጥቶብናል በሚል በጨዋታው ላይና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅሬታ አሰምተዋል። በአጠቃላይ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በስታዲየም ገብቶ የተከታተለ ተመልካች ብዛት አነስተኛ ነበር። ዛሬ መካሄድ የነበረባቸው የወላይታ ዲቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና የሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ተስተካካይ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በቅደም ተከተል በአዲስ አበባ ስታዲየምና በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት እንደሚካሄድ የኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 48 ነጥብ፣ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቀሌ ከተማ በ46 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮ-ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማ እና መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ናይጄሪያዊው የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኦኮኪ አፎላቢ በ17 ግቦች እየመራ ሲሆን፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ- አሌትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም