በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችለን ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል - አንጋፋ አትሌቶች

61
አዲስ አበባ ጥር 17 ቀን 2012  (ኢዜአ ) በዘላቂነት ለሟቋቋም የሚያስችለን ድጋፍ ሊደረግልን ይገባሰል ሲሉ አንጋፋ አትሌቶች ጠየቁ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በተቻለው መጠን ለአንጋፋዎቹ አትሌቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሆነና አትሌቶቹ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የማድረግ ሃላፊነት ግን የፌዴሬሽኑ ብቻ እንዳልሆነ አስታውቋል። 37ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ዛሬ ተካሄዷል። ኢዜአ በአንጋፋ (ቬትራን) አትሌቶች በ8 ኪሎ ሜትር ውድድር ተሳታፊ አትሌቶቹን አሁን ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል። የ70 ዓመቱ አንጋፋ አትሌት ገብረጻዲቅ ገብረስላሴ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ በ5 እና 10 ሺህ እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች ላይ እንደሮጡ ያወሳሉ። በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ በኬንያና በሱዳን በተካሄዱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አድርገዋል። አትሌት ገብረጻዲቅ ለኢትዮጵያ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ "ተሳትፎ ያደረጉ አንጋፋ አትሌቶች ተረስተናል፤ በቂ ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም" ብለዋል። አንጋፋ አትሌቶችን ባቀፈው ማህበርም ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የአልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ ቢያገኙም ህይወታቸውን የሚቀይር እንዳልሆነ ገልጸዋል። የአምስት ልጆች አባት እንደሆኑና ልጆቻቸው በሚያደርጉላቸው የተወሰነ ድጋፍ በአነስተኛ ደረጃ በሚገኝ የሲሚንቶ ሽያጭ ላይ ቢሰማሩም ህይወታቸውን ለመምራት በቂ አይደለም ሲሉ ነው አትሌት ገብረጻዲቅ የተናገሩት። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፣መንግስትና ህብረተሰቡ ለአገር ኩራት ለሆኑ አንጋፋ አትሌቶች ዘላቂነት ያለውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል። የ82 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አትሌት መቶ አለቃ ታደሰ ሰጥአርጋቸው በበኩላቸው በ1960 ዓ.ም በባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ የአትሌቲክስ ቡድን በ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ህይወታቸውን እንደጀመሩ ያወሳሉ። ከዚያም በኋላ መቶ አለቃ ታደሰ በሩሲያ (በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት)፣ግሪክ፣ቻይና፣በፖርታሪኮ ፣ጅቡቲ፣ በታንዛንያ፣ዛንዚባር፣አልጄሪያ፣በቻይናና ካናዳ በተካሄዱ የግማሽ ማራቶንና ማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ደረጃ ውስጥ በመግባት ለአገራቸው ውጤት እንዳስመዘገቡም ይናገራሉ። የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አንጋፋው አትሌት በጡረታ ከአዲስ አበባ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር በሚያገኙት ድጎማ ኑሯቸውን እየመሩ እንደሆነ ገልጸዋል። የስፖርቱ ቤተሰብ "ለአገር ውለታ የሰሩ አትሌቶችን ማስታወስ አለበት፤ የት ናቸው? ብሎ ጠይቆ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበትም" ብለዋል። የአዲስ አበባ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ወገኔ ሲሳይ በበኩላቸው በማህበሩ 118 የሚሆኑ አንጋፋ አትሌቶች እንዳሉ ይገልጻሉ። ማህበሩ ለአትሌቶቹ በማህበሩ ካለው መዋጮና ከሌሎች አካላት አትሌቶቹ ሲታመሙ ለህክምና ድጋፍና ለሞቱ አትሌቶች ቤተሰቦችም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ያ ግን በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያን በተለያዩ መድረኮች ካስጠሩ አትሌቶች መካከል በመንገድ ላይ የወደቁ አሉ ይላሉ፤ አነስተኛ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች የተሰማሩም እንዳሉ ጠቅሰዋል። ለአገር አስተዋጽኦ ያደረጉ አትሌቶች መረሳት አንደሌለባቸውና መንግስት፣አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑና የሚመለከተው አካልም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አቅም በፈቀደ መልኩ ለአንጋፋ አትሌቶቹ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጻለች። ፌደሬሽኑ በግንቦት 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር እንዲቋቋም በማድረግ ለማህበሩ የተለያዩ የቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን በማውሳት። ፌዴሬሽኑ ለማህበሩ በየዓመቱ የ100 ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሳለች። በውጭ አገራት ከሚገኙ አንጋፋ አትሌቶች ገንዘብ በማሳባሰብ አትሌቶቹ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነውም ብላለች። በዘላቂነትም አትሌቶቹን የማቋቋም ተግባር የፌዴሬሽኑ  ሃላፊነት ብቻ እንዳልሆና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ የገለጸችው። ማህበሩም አንጋፋ አትሌቶቹ በዘላቂነት ሊቋቋሙ የሚችሉበትን ዝርዝር እቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባውና ይሄንንም እቅድ ተከትሎ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ተናግራለች። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታላቅ ውለታ የዋሉትን አንጋፋ አትሌቶች በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም የሚመለከተው አካል በተቀናጀ መልኩ መስራት እንዳለበትም አሳስባለች። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም በየዓመቱ ለአንጋፋ አትሌቶች ማህበር የ200 ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ገልጸዋል። የቀድሞዋ የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌት ፋንቱ ሚጌሶም ዛሬ ለማህበሩ የ30 ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረገች ጠቅሰዋል። ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴም በተያዘው ዓመት የ100 ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረጉም አውስተዋል። አትሌት መልካሙ ተገኘም በግሉ ተነሳሽነት ለአንጋፋ አትሌቶች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግና ዛሬም የሶስት ሺህ ብር ድጋፍ እንዳደረገም አመልክተዋል። አንጋፋ አትሌቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም ብዙ መስራት አንደሚጠይቅና ሁሉም አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ ቢልልኝ ጠይቀዋል። በዛሬው የአንጋፋ አትሌቶች ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አትሌቶች የ4ሺህ፣3ሺህ እና 2 ሺህ 500 ብር ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም