የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፊፋ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ውጪ ሆነ

146
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012  የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፊፋ ከ17 ዓመት የሴቶች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ውጪ ሆኗል። ህንድ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም በምታስተናግደው ሰባተኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ የመልስ ጨዋታዎች ተደርገዋል። ዛሬ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የማጣሪያ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አቻው 3 ለ 1 ተሸንፏል። ጁሊየት ናሉኬንጌ ሁለት ፣ማርጋሬት ኩኒሂራ አንድ ግብ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አስቆጥረዋል። አረጋሽ ካልሳ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማስተዛዘኛውን ግብ አስቆጥራለች። ጁሊየት ናሉኬንጌ በዩጋንዳ በተካሄደው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠሯ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በካምፓላ ስታርስ ታይምስ ስታዲየም አድርጎ በዩጋንዳ አቻው 2 ለ 0 መሸነፉ አይዘነጋም። በአጠቃላይ ድምር ውጤት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አቻው 5 ለ 1 ተሸንፎ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ውጪ ሆኗል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት የዝግጅት ጊዜ ማነስ በቡድኑ ላይ የውጤት ተጽእኖ እንደሚያመጣ ገልጾ እንደነበር አይዘነጋም። በአንጻሩ በአሰልጣኝ አዩባ ከሊፋ የሚሰለጥነው የዩጋንዳ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የማሳተፍ ኮታ አላት። በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ። በሌላ የእግር ኳስ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህርዳር ከተማን አስተናግዶ ኸይደር ሸረፋ ባስቆጠራት ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል። በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ፤በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን እንዲሁም በዝዋይ ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0  አሸንፈዋል። በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል። ትናንት በተደረጉ የፕሪሚየር ሊጉ የ10 ሳምንት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ የሊጉን መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታን 1 ለ 0 ሲረታ፣ ሰበታ ከተማ ደግሞ ሀዋሳ ከተማን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ሸነፉ ይታወሳል። ስሑል ሽረ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወልቂጤ ከተማ በስታዲየም እድሳት እንዲሁም ሰበታ ከተማ በስታዲየም ግንባታ ምክንያት ጨዋታቸውን በሌላ ሜዳ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ19 ነጥብ  ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ በ18 ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ወልቂጤ ከተማ፣ድሬዳዋ ከተማና  ሀዲያ ሆሳዕና ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በአስር ግቦች ሲመራ፣ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የባህርዳር ከተማው ፍጹም አለሙ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም