በፕሪሚየር ሊጉ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል

61

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012 በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻው የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሶዶና አዲስ አበባ ላይ ተደርገዋል።

ሶዶ ላይ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉን አሸናፊ ወላይታ ድቻን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 ረቷል።

በአምናው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በአንድ ነጥብ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ሁለቱ ክለቦች የዛሬው ጨዋታቸው በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ የሚጠበቅ ነበር።

አምና በአንድ ነጥብ ተበልጦ የሊጉን ዋንጫ ያጣው መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ተቀናቃኙን ወላይታ ድቻን ማሸነፍ ችሏል።

ውጤቱንም ተከትሎ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ነጥቡን ወደ 17 ከፍ በማድረግ መሪነቱን ያጠነከረ ሲሆን የአንደኛ ዙርን ውድድር በመሪነት አጠናቋል።

በአንጻሩ ወላይታ ድቻ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየምም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የሶስት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ሙገር ሲሚንቶ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን 3 ለ 1 አሸንፏል።

ሙገር ሲሚንቶ ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 17 ከፍ በማድረግ ከመሪው መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በግብ ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የአንደኛውን ዙር ውድድር አጠናቋል።

በሌላ ጨዋታ መከላከያ ጣና ባህርዳርን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 ያሸነፈ ሲሆን ጣና ባህርዳር በሊጉ ያደረጋቸውን ስድስቱንም ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዷል።

ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ላይ ይጫወታሉ።

በአራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሶዶ ላይ መካሄድ የነበረበትና ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመው የወላይታ ድቻና መከላከያ ተስተካካይ ጨዋታም በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል።

ከሁለቱ ክለቦች ውጪ የተቀሩት ክለቦች የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብራቸውን በዚህ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች እንደሚያጠናቅቁ ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል።

በወንዶች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 48 ለ 40 አሸንፏል።

ውቅሮ ላይ ሀዋሳ ከተማ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮን 89 ለ 65 ረቷል።

በሴቶች ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ጎንደር ከተማን 42 ለ 33፣ ጅማ ላይ ሀዋሳ ከተማ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጅማ ከተማን 73 ለ 47 አሸንፈዋል።

በወንዶች ጎንደር ከተማ፣ በሴቶች የካ ክፍለ ከተማና ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ ያላደረጉ አራፊ ክለቦች ናቸው።