የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለአሜሪካዊዉ ሚስተር ማርክ ገልፋንድ የክብር ዶክትሬት ሰጠ

68
ባህርዳር ኢዜአ ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እውቀትን በትምህርት ቤቶች በማስፋፋት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ላላቸው አሜሪካዊው ምሁር ሚስተር ማርክ ገልፋንድ የክብር ዶክትሬት መስጠቱን አስታወቀ። ለግለሰቡ ትናንት የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው በኢትዮጵያና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ለማሳደግ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ተብሏል። ታዳጊ ህጻናት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በሒሳብና በእንግሊዘኛ የትምህርቶች መስኮች ላይ በማተኮር የቀጣይ ሳይንቲስት እንዲሆኑ አልመው መስራታቸው ለክብር ዶክትሬት እንዳበቃቸው ተገልጿል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት ሚስተር ማርክ  የተፈጥሮ ሳይንስ  ትምህርቶች  የሚጠይቁትን የቤተሙከራ፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችንና ሌሎች ግበአቶችን በማሟላት እያገዙ ነው። ለዚህም "ገልፋንድ በጎ አድራት ድርጅት" የተሰኘ ተቋም መስርተው በአሜሪካና እስራኤል የሳይንስ ማዕከላትን በማቋቋም ሲሰሩ የቆዩ ናቸው ብለዋል ። ባለፉት 10 ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳና ኬንያ ህጻናትና ታዳጊዎች ላይ በመስራት ተሰጥአኦ ያላቸውን የሳይንስ ተመራማሪዎች ለማውውጣት እየጣሩ የሚገኙ ናቸው ተብሏል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ከስምንት ዓመት በፊት በ13 ሚሊዮን ብር  ወጪ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሂሳብ(STEM) ማዕከል በማስገንባት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በየዓመቱ 50 ተማሪዎችን እየተቀበለ በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ በስነስርዓቱ ላይ ተገልፇል "ሚስተር ማርክ ገልፋንድ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር ለመተርጎም  እየለፋ ያለ ድንበር የማይገድበው  ቅን  እውቀት ናፋቂ  ግለሰብ ነው ያሉት" ደግሞ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር  ማስረሻ ፈጠነ ናቸው። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ግለሰቡ ካበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር ሲታይ የሚገባው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲውን ማመስገን ተገቢ ነው ብለዋል ። "አለምን የተሻለ ለማድረግ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን  በሚገባ አውቆ ተግባር ላይ ማዋል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው"  ያሉት ደግሞ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚው የፊዚክስ ምሁር ሚስተር ማርክ ገልፋንድ ናቸው። "ተማሪዎች ከፍተኛ ትምህርት ከመድረሳቸው በፊት የሳይንስ ትምህርቶችን  በንድፈ-ሃሳብምና በተግባር እያወቁ ማደግ አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። "የኔ አላማ ባለኝ አቅም የሳይንስ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የቤተ ሙከራ፣ የኮምፒተር ማዕከል፣ ቤተ መጻህፍትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማሟላት በትህርት አሰጣጡ ዙሪያ  ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ መስራት ነው " ብለዋል ። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሰጣቸው የክብር ዶክትሬት መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከ25 በላይ የሳይንስ ማዕከላትንና ሁለት የሳይንስ ሙዜሞችን በመቀሌና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች መገንባታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ ። ሚስተር ማርክ ገልፋንድ እንደ እስራኤል ባሉ የመካከለኛው ምስራቅ ተንቀሳቃሽ የሳይንስ ማዕከል አቋቁመው 200 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆነም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም