በፋብሪካው የሚሰሩ አካል ጉዳተኛ ሰራተኞቸ የስራ ታታሪነት ከሁሉም የላቀ ነው - የደብረ ብርሃን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ

74
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012 በፋብሪካው የሚሰሩ አካል ጉዳተኞች ያላቸው የስራ ታታሪነት ከሁሉም ሰራተኞች የላቀ መሆኑን በደብረ ብርሃን የሚገኝ አንድ የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገለጸ። በፋብሪካው የሚሰሩ አካል ጉዳተኞችም ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ለአካል ጉዳተኞች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የእንጨት ፋብሪካውን ተሞክሮ አንዲወስዱ ጠይቀዋል። ግሩም ጉራራና ገነት ጉራራ ደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኝና ባለቤትነቱ የአማራ ክልል መንግስትና የቻይና ባለሀብቶች ጥምር በሆነው የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ መስማት የተሳናቸው ሰራተኞች ናቸው። ወጣት ግሩም ጉራራ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ 12 መስማት የተሳናቸው ማኅበራትም ሊቀ መንበር መሆኑን ገልጿል። አሁን በሚሰራበት የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካም ከሚገኙ የኮንትራት ማኅበራት መካከል አንዱ እርሱ አባል የሆነበትና 9 መስማት የተሳናቸው ሰራተኞችን ያቀፈው ማህበር መሆኑን ገልጿል። በግሉም ሌሎች ፋብሪካዎች ላይ መስራቱን አስታውሶ፣ አሁን የሚሰራበት ፋብሪካ ከሌሎቹ ፋብሪካዎች በተለየ አካል ጉዳተኞችን እኩል ከማሳተፉና ከስራ እድል ፈጠራው በተጨማሪም ሰራተኞች እንጨት እንዲወስዱ እድል ማመቻቸቱን ይገልጻል። ይሀን በማድረጉም አካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ቤተሰብ እንዲመሰርቱና ኑሯቸውን በቅጡ እንዲመሩ ማድረጉን ነው የሚናገረው። በተመሳሳይም በፋብሪካው ውስጥ መስራት ከጀመረች አምስት ዓመታት ያስቆጠረችው ወጣት ገነት ጉራራ ፋብሪካው ውስጥ በመስራቷ አዕምሯዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማመጣቷን ትናገራለች። አካል ጉዳተኛ ተሁኖም ማንኛውንም ስራ መስራት እየተቻለ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ግን የተዛባ መሆኑንም ይናገራል። አካል ጉዳተኛ እንደማንም ሰው እውቀት ያለውና የተሰጠውን ስራ ከማንም በላይ መስራት እንደሚችል በመግለጽ፣ ሌሎች ፋብሪካዎችም ከዚህኛው ፋብሪካ ተሞክሮ በመውሰድ አካል ጉዳተኞችን አሳታፊ እንዲያደርጉ ወጣት ግሩም ይጠይቃል። የደብረ ብርሃን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ደጀኔም ፋብሪካው ከፈጠረው ከ352 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል በተጨማሪ፣ በማህበር የተደራጁ 19 ማህበራትን በተለያዩ የስራ መስኮች ያሰራል። ከእነዚህ ማኅበራት መካከልም አንዱ መስማት የተሳናቸው መሆኑን ገልጸው፤ "የሰራተኞቹ ታታሪነት ግን ከሁሉም ማኅበራት የተለየ ነው" በማለት ስራ ወዳድነታቸውን መስክረዋል። "ሰራተኞቹ ጸብና ወሬ አያውቁም፤ ቀጥታ ስራ ላይ ብቻ ያተኩራሉ" ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በፋብሪካው ተሞክሮ አካል ጉዳተኝነት ታታሪነትን እንጂ ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ የሚያጎድሉት ነገር አለመኖሩን ነው የተናገሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም