የባህል ስፖርት ጨዋታዎች የህብረተሰቡ ማህበራዊ ትስስር ያጠናክራሉ ተባለ

71

ደብረማርቆስ ኢዜአ ጥር 17 /2012  የባህል ስፖርት ጨዋታዎች የህብረተሰቡን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ሲል የአማራ ክልል የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ገለፀ ። 17ኛው የአማራ ክልል የባህል ስፖርት ውድድርና 13ኛው የባህል ፌስቲባል በደብረማርቆስ ከተማ አጀጋጅነት ዛሬ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለሙ ሁነኛው በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የባህል ስፖርት ውድድሩ የየአካባቢውን ባህል፣ ወግና እሴት በማበልጸግ ውጤት እያስገኘ ነው።

 ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በሚወዳደሩበት የስፖርት ዘርፍ ራሳቸውን በማዘጋጀት  የሚያሸንፉበትና በአገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን የሚወክሉ ብቁ ተወዳዳሪዎች የሚመረጡበት መድረክ  ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል።

ስፖርተኞቹ የአካባቢያቸውን አለባበስ፣ አጨፋፈርና ሌሎች ባህሎችን በማቅረብና ልምድ በመለዋወጥ የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ለባህላዊ ስፖርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ በተካሄዱ ውድድሮች የበላይ ሆኖ ማጠናቀቁንም ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ጌትነት ተስፋው በበኩላቸው ወድድሩን በስኬት ለማጠናቀቅ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከመስተንግዶ ጀምሮ እስከ መወዳደሪያ ቁሳቁሶችና ሜዳዎች ዝግጅት ተደርጓል።

የውድድር ዓይነቶችም በገና፣ በትግል፣ በገበጣ፣ በሻህ፣ በቡብ፣ በፈረስ ሽርጥ፣ በፈረስጉግስ፣ በኮርቮ እና በቀስት ስፖርት የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውድድሩ ከ630 በላይ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎችና የውድድር አመራሮች ደብረ ማርቆስ መግባታቸውን ተረጋግጧል ።

ከደቡብ ጎንደር ዞን የመጣው ወጣት ፍትህአለው ብርሃኑ እንዳለው በውድድሩ አሸናፊ በመሆን በሁሉም ጨዋታዎች ዋንጫ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

 የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የባህል ስፖርት አሰልጣኝ አቶ ተስፋ ዘገየ በበኩላቸው “ባለፈው ዓመት በራሳችን ዞን  አስተናጋጅነት ሁለተኛ ደረጃን አግኝተን ጨርሰን ነበር” ብለዋል።

በዚህ ዓመት ደግሞ የአንደኝነት ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ቅድም ዝግጅት አድርገናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

ከጥር 17እስከ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በ10 ስፖርት አይነቶች እየተካሄደ የሚቆየው ይኽው ውድድር ዛሬ ጧት በምስራቅ ጎጃምና በዋግ ኽምራ ዞኖች መካከል በተካሔደው የገና ጨዋታ ተጀምሯል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም