7 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ... ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

62
አዲስ አበባ ጥር 17 /2012 (ኢዜአ) በሀገሪቱ እስከ ሰኔ 2012  7 ሚሊዮን ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ከጥር እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የድጋፍ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎችን በጥናት መለየቱንም አስታውቋል። በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በጥናቱ መሰረት ለሰብዓዊ ድጋፉም 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው። በአሁኑ ወቅት በምግብ ፍላጎት ተረጂ የሆኑት 6 ሚሊዮን ሰዎች እንደሆኑና ባለፈው ዓመት ከነበረው 8 ሚሊዮን ተረጂ ጋር ሲነጻጻር ቁጥሩ መቀነስ ማሳየቱንም ተናግረዋል። የዚህ ምክንያት ደግሞ በመኽር ምርት የተሸፈኑ የሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በመኽር ምርት ግኝት ለማገገም በመቻላቸው ነው ተብሏል። የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር የሚወሰነው የሰብዓዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት ሰነድ በማዘጋጀት እንደሆነም ጠቁመዋል። በአገሪቷ ከቀደመው ጊዜ በተለየ የድርቅ ክስተት እየተደጋገመ በመምጣቱ የህዝቡን አኗኗርና የአገሪቷን ኢኮኖሚ እየጎዳ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት በአገሪቷ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ ድርቁን ተደጋጋሚ አድርጎታልም ብለዋል። መንግስት ጉዳቱን ለመከላከልና ለመቋቋምም ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየሰራ መሆኑን አስታውሰዋል። ለችግሩ ወቅታዊ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎንም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር አደጋውን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ዘላቂ የልማት ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም