37ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ተካሄደ

90
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012 37ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ዛሬ ተካሄዷል። በውድድሩ ላይ አራት ቻይናውያን አትሌቶች ተሳትፈዋል። በዛሬው የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶችና 8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም የ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ (ሴትና ወንድ) የዱላ ቅብብል ውድድሮች ተካሄደዋል። በተጨማሪም በ8 ኪሎ ሜትር የአንጋፋ አትሌቶች ውድድርም ተካሄዷል። በውድድሩም በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች አትሌት በቀለች ተክሉ በ21 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ17 ማይክሮ ሴኮንድ አሸንፋለች። የአማራ ክልል ተወዳዳሪ የሆነችው አትሌት መልኣክናት ውዱ 21 ደቂቃ ከ33 ሴኮንድ ከ88 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ፣ አትሌት አሚናት አህመድ ከሐዋሳ ከተማ በ21 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ከ64 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች። በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች ደግሞ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከሱር ኮንስትራክሽን በ24 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ56 ማይክሮ ሴኮንድ አሸንፏል። የአማራ ክልል ተወዳዳሪ የሆነው አትሌት በረከተ ዘለቀ በ24 ደቂቃ ከ47 ሴኮንድ ከ4 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ፣ ሌላኛው የአማራ ክልል ተወዳዳሪ አዲስ ይሁኔ 24 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ ከትግራይ ፖሊስ በ35 ደቂቃ ከ6 ሴኮንድ ከ78 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን የመሰቦ ሲሚንቶ ተወዳዳሪ የሆነችው አትሌት ፎይተን ተስፋይ በ35 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ8 ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥታለች። አትሌት ሹሬ ደምሴ ከኦሮሚያ ፖሊስ በ35 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ከ42 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች አትሌት ንብረት መልኣክ ከአማራ ክልል በ30 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ62 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል። አትሌት አስረሴ ጌታሁን ከአማራ ማረሚያ በ31 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ89 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ፣ የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪ የሆነው አትሌት ዲዳ ለማ በ31 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ ከ61 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥቷል። በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ (ሴትና ወንድ) የዱላ ቅብብል የኦሮሚያ ክልል፣ ኦሮሚያ ውሃ ስራዎችና አዳማ ከተ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በአንጋፋ(ቬትራን) አትሌቶች በ8 ኪሎ ሜትር ከ50 ዓመት በላይ አትሌት አያሌው እንዳለ፣አትሌት ተስፋዬ ጉታና አትሌት ሃይሌ ቆርቾ ከአንድ እስከ ሶስት ወጥተዋል። በ8 ኪሎ ሜትር ከ50 ዓመት በታች የአንጋፋ(ቬትራን) አትሌቶች ውድድር አትሌት ደሳለኝ ተገኝ፣አትሌት ግርማ ወርቁና አትሌት ገዛኸኝ ገብሬ ከእንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በውድድሩ ላይ አራት ቻይናውያን አትሌቶች በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ተሳትፈዋል። ዱኦ ቡጂ፣ ሱ ላንግ ካልረን፣ ሚጁ ኒማና ዳንሙዤን ቺዋንግ በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ቻይናውያን አትሌቶች ናቸው። የአማራ ክልል በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶችና 8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች ውድድር በቡድን የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ሽልማት አግኝቷል። የኦሮሚያ ክልል በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ (ሴትና ወንድ) የዱላ ቅብብል በቡድን አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። በወጣት ወንዶችና ሴቶች ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አትሌቶች የ11 ሺህ፣ የ9 ሺህ እና የ7 ሺህ ብር ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን እንዲሁም በአዋቂ ሴቶችና ወንዶች ከእንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለያዙ የ22ሺህ፣16ሺህ እና 11 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል። በአጠቃላይ በውድድሩ ለተሳተፉ ተወዳዳሪዎች የ400 ሺህ ብርና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ በቀለ ሆርዶፋ እንዲሁም ሌሎች የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት አበርክተዋል። ለውድድሩ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላትም የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በውድድሩ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ከተቋማት፣ ከክለቦች የተውጣጡና በግል ከ800 በላይ አትሌቶች መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም