በደቡብ ወሎ ዞን በ1 ሺህ ተፋሰሶች የአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተጀመረ

119
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012 በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ በበጋው ወቅት በ1ሺህ ተፋሰሶች ላይ የሚካሄደውን የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ስራ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትናንት ተጀመረ። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ እንደገለጹት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተራቁተው የነበሩ መሬቶች አገግመው ምርት መስጠት ጀምረዋል። በዚህም የደረቁ ምንጮች በመፍለቃቸው፣ መሬቱ ልምላሜ በመልበሱና የደን ሽፋኑ እየጨመረ በመምጣቱ በእንሰሳት እርባታ፣ በመኖና በንብ ማነብ ስራ በመሰመራት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ አየሆነ ነው ብለዋል ። የተገኘውን ጥቅም ለማስቀጠልም በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ600 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ  ከአንድ ሺህ በላይ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ማካሄድ መጀመሩን ተናግረዋል። በተፈጥሮ ሃበት ስራው ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚለማ ሲሆን በቅድመ ዝግጅት ከ50 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮችን በማሰልጠን ስራውን በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማከናወን ተችሏል ። ለአንድ ወር የሚቆየው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ለየት የሚያደርገው በጎርፍ የተጎዱ መሬቶችንና በተራቆቱ ተራሮች ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ፤ የሳርና የችግኝ ተከላ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራን በማጠናከር ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠሪያ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል። ወጣቱ ትውልድም የለማውን ተፋሰስ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት በእንስሳት፣ በንብ ማነብ፣ በመኖ አቅርቦትና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በመሰማራት ህይወቱን ለመቀየር ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ034 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል አካባቢያቸው ተራራማና ኮረብታማ በመሆኑ በልፋታቸው ልክ ምርት ካለማግኘታቸውም ባለፈ ለእንሰሳት መኖ ይቸገሩ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ በየዓመቱ በተሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አካባቢያቸው በመልማቱ የእንሰሳት መኖ በቀላሉ በማግኘታቸው ከብቶቻቸውን አስረው በመቀለብ በወተት ልማትና አድልበው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል ። ሌላዋ አርሶ አደር ወይዘሮ አስያ ይመር እንደተናገሩት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የማሳቸውን የአፈር ለምነት በመመለሱ ቀደም ሲል ከ15 ኩንታል በታች ያገኙበት የነበረው መሬት አሁን ላይ ከ25 ኩንታል በላይ እንዲያገኙ አስችሎአቸዋል። በዞኑ ከ2003 ዓም ጀምሮ ከ3 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ከ800 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ሆኖ መልማቱን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም