በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ዙሪያ ለአካባቢ ልማትና ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ተሰጠ

60
ጋምቤላ ኢዜአ ጥር 17 /2012  በጋምቤላ ክልል ለስደተኞች ከሚሰጠው የሰብአዊ አገልግሎቶች ጎን ለጎን ለተፈጥሮ ሀብታ ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጎብኝተዋል ። የምክር ቤቱ አባላት ለኢዜአ እንደተናገሩት ለስደተኞች ከሚደረገው የሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ፣ በጸጥታና ሌሎች ዘርፎችም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል። ከአባላቱ መካከል አቶ ተስፋየ ሮበሌ እንዳሉት ለስደተኞች የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች ሰብአዊ አገልግሎቶችን በማቅረበ ረገድ መልካም ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ለስደተኛቹ የኃይል አመራጭ ባለመቅረቡና የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ በተፈጥሮ የደን ሃብቱ ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል። ስልሆነም በመጠለያ ጣቢዎች አካባቢ እየተሰሩ ያሉት የደን ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል ። በአካባቢው አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግሮች ሲከሰቱ ከስደተኞች ጋር የማያያዝ ዝንባሌዎች እንዳሉ መገንዘባቸውን ገልጸው ችግሮች ለመከላከልና የህግ የበላይነት ለማስከበር የሰደተኞች አስተዳደርና ሰላም  ሚኒስቴር ተቀናጅተው የተጠናከሩ ስራዎች ሊያከናወኑ ይገባል ብለዋል። ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አስካል ጥላሁን በበኩላቸው  በምክር ቤቱ ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት አዋጅ መፅደቁን ገልፀዋል ። በአዋጁ መሰረት በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ ተግባራዊ ከሚደረጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም ስደተኞች አገራቸው ሰላም ሆኖ እስኪመለሱ ድረስ መረሃ ግብሩን ተግባራዊ በማድረግ የልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው  ወይዘሮ አስካል አሳስበዋል ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ለምክር ቤቱ አባላቱ እንደገለፁት አዋጁ ከመጽደቁ በፊትም ሆነ ከጸደቀ በኋላ ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ባለመቻሉ ሊተገበሩ የታሰቡት የልማት ፕሮጀክቶች በተፈለገው ልክ አልሄዱም ብለዋል። በመሆኑም የስደተኞች አስተዳደር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከአመራሩ ጀምሮ እስከ  ህብረተሰቡ የዘለቀ የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል። በስደተኞችና ከስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ኤጀንሲ የምዕራብ ክልል የስደተኞች ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የፕሮቴክት ኃላፊ አቶ መዝገበ ገብረ ማሪያም እንደሚሉት ደግሞ በምክር ቤት አባላት የተጠቀሱን ክፍተቶች ለማረም እንሰራለን ብለዋል። በተለይም ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ምላሽ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የግንዛቤ ክፍቶች ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል ። በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች 420 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞ ተጠልልው እንደሚገኙ ከማስተባበሪያ ጽህፍት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም