አለአግባብ የተያዙ ሼዶችና ኮንቴይነሮች ቅሬታ አስከተሉ

63

ደሴ ኢዜአ ጥር 17 ቀን 2012 ዓም  በደሴ ከተማ ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጥሩ የተሰሩ ሼዶችና ኮንቴይነሮች ለ15 ዓመታት አለአግባብ በግለሰቦች እጅ እንዲቆዩ መደረጉ ለሌሎች ወገኖች የስራ እድል እንዳይፈጠር እንቅፋት በመሆናቸው የከተማዋ ወጣቶች ቅሬታቸውን አሰሙ ።

በህገ ወጥ መንገድ የተያዙትን ኮንቲነሮችና ሸዶች በማጣራት ማስለቀቅ መጀመሩን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ያብባል ደጀኔ እንደገለፀው የሥራ እድል ለማግኘት ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ከተደራጀ ሁለት ዓመት ቢሆነውም የስራ አማራጭ እንዳልተፈጠረለት ይናገራል ።

 “በየዓመቱ ከመመዝገብና ከመደራጀት ውጭ ስራ ማግኘት ባለመቻሌ በቤተሰብ ጥገኝነት ስር ሆኖ መኖር ተስፋ እንድቆርጥና ለአዕምሮ ጭንቀት እንድዳረግ አድርጎኛል ” ብሏል፡፡

 ምክንያቱ ደግሞ ለስራ አጥ ወጣቶች የተሰሩ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችና ኮንቴይነሮች የወሰዱ ሰዎች በህጉ መሰረት ለ5 ዓመታት ሰርተው ሀብት በማፍራት ለሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች ማስተላለፍ ሲገባቸው አለአግባብ ከ15 ዓመታት በላይ እንዲጠቀሙበት በመደረጉ እንደሆነ ወጣት ያብባል ተናግሯል ።

ለስራ አጥ ወጣቶች የተገነቡ ሸዶችና ኮንቴይነሮች ለረጅም ጊዜ በግለሰቦች እጅ መያዛቸው አግባብ አይደለም ያለው ደግሞ የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰይድ ሙህዬ ነው፡፡

ሼዶችና ኮንቴይነሮች የተሰጣቸው ግለሰቦች እስከ አምስት ዓመት ድረስ ብቻ ሰርተው ሀብት ካፈሩ በኋላ የራሳቸውን አማራጭ በመጠቀም ለሌሎች እንዲያስተላልፉ መመሪያ  ቢደነገግም ከባለሙያዎችና ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመተሳሰር ህግ ተጥሶ አለአግባብ እንዲበለፅጉበት እየተደረገ መሆኑን አስረድቷል ።

 መንግስት በህገ ወጥ መንገድ የተያዙትን ኮንቴይነሮችና ሼዶችን በማስለቀቅ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች እንዲተላለፉ ወጣቱ ጠይቋል ።

 የደሴ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ምንይሻው በሪሁን በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ወጣቶቹ የሚያነሱትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ መውሰድ እንደተጀመረ ተናግረዋል ።

ኮሚቴ ተቋቁሞ ባካሄደው ማጣራትም ኮንቲነሮችንና ሸዶችን ያከራዩ፣ መኖሪያ ቤት ያደረጉ፣ ለሌላ ያስተላለፉ፣ ዘግተዉ የጠፉና በስማቸው ለማዛወር የሚያማትሩ መኖራቸውን ተረጋግጧል።

 በህገ ወጥ መንግድ የተያዙ 176 ሼዶችና ኮንቴይነሮች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 58ቱን በማስለቀቅ ለስራ አጥ ወጣቶች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

 በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ባሉበት ከተማ ኮንቴይነሮችንና ሸዶችን ከ15 ዓመት በላይ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው እንዲቆዩ መፍቀድ የአመራሩ ዝርክርክርነትና እንዝህላልነት ማሳያ በመሆኑ አሁን ላይ በቁርጠኝነት የህግ ማስከበር ስራው የተጀመረ መሆኑን ከምክትል መምሪያ ኃላፊው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

 በደሴ ከተማ ከ400 በላይ ኮንቲነሮችና ሼዶች በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለ28 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ቢያቅድም በተጠቀሱትና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ያከናወነው ግን ከ4 ሺህ የዘለለ አይደለም ተብለሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም