ኢዜማ በሆሳዕና ከተማ ከአባላቱ ጋር ተወያየ

55
ሆሳዕና፤  ጥር 16/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊና ፍትህ ፓርቲ/ ኢዜማ/ዛሬ በሀድያ ዞንና አካባቢው ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር በሆሳዕና ከተማ ተወያየ፡፡ የኢዜማ ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትን በመፍጠር ዜጎች በሰላም የሚኖሩባትን ሀገር መገንባት የፓርቲው ዓላማ ነው። የፓርቲው ግብ ስልጣን መያዝ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ " የሀገሪቱን ሉአላዊነት በማስከበር መሪዎች ከህዝብ ጋር ተባብረው የሚሰሩበትን ስርዓት መፍጠር ነው "ብለዋል፡፡ ለዚህም የሀገር ሰላም መረጋገጥ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ኢዜማም ይህን ለማሳካት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል። ቀጣዩን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በማድረግ የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ አባላቱ ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ አበበ አሳስበዋል። “ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝነት በማረጋገጥ ለመብቱ ሰላማዊ ትግል ማድረግ አለበት “ ያሉት ደግሞ  በኢዜማ  የሀድያ ዞን ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ነጋሽ ደስታ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም