ፅዱ ኢትዮጵያ የዘመቻ መርሃ ግብር በቀጣዮቹ አምስት አመታት እንደሚተገበር ተገለፀ

81

አዲስ አበባ፤ ጥረ 16/2012(ኢዜአ) ፅዱ ኢትዮጵያ የዘመቻ መርሃ ግብርን በመተግበር መንገድ ላይ የመፀዳዳት ልማድን በፈረንጆቹ 2024 ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ስራዎች መጀመራቸው የውሃ ልማት ኮሚሽን ገለፀ። የውሃ ልማት ኮሚሽን በአዋጅ 1097/2011 የተቋቋመ ሲሆን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሠረተ-ልማት አስተዳደር ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ የኢትዮጵያን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ከዓላማዎቹ መካከል አንዱ ነው።

ኮሚሽኑ የገጠር ሳኒቴሽን ዘመቻ እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2024 ዶክመንት ዝግጅት መጠናቀቁንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጿል።

የውሃ ልማት ኮሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩን ከፈረንጆቹ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በመተግበር  በመንገድ ላይ የመፀዳዳት ልማድን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ታስቧል።

በመንገድ ላይ መፀዳዳት የአገር ገፅታን ከማበላሸት በተጨማሪ የጤና ችግር የሚያስከትል በመሆኑ ዘመቻውን በማድረግ የኅብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር እንደሚሰራ ዶክተር በሻህ ገልጸዋል። በዘመቻ መርሃግብሩ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎችን በመጠቀም በኅብረተሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከአመለካከት ለውጥ ስራው ባሻገር መጸዳጃ ቤት የሌላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች እንዲገነባላቸው እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

መርሃ ግብሩ 50 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀው፤ በጀቱ በመንግስት፣ በአጋር ድርጅቶችና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሸፈን መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ያላት ማህበራዊ ትስስርና ህዝቡን በማነሳሳት ዘመቻውን ቀድማ የማሳካት አቅም እንዳላትም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም