የቱሪስት መስህቦች ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠበቀው አስቸኳይ እድሳት ሊደረግባቸው ይገባል-የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት

69
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ በቅርቡ የእድሳት ስራ ሊደረግባቸው እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ቋሚ ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል የጎሬ የኢንግሊዝ ቆንስላ፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግስትና ጅማ ሙዝየም፤ በደቡብ ክልል የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም፣ ጥንታዊው የቶንጎላ መስጊድ፣ የአንድራቻ መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች የመስክ ጉብኝት ሪፖርቱን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቅርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የጎሬ የኢንግሊዝ ቆንስላ ህንፃ ታሪካዊ ቅርስ "ይዘቱን የሚያጠፋ አደጋዎች እየደረሱበት ይገኛሉ" በመሆኑም ከወረዳ እስከ ዞን ያለው አመራር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከክልሉ ጋር በቅንጅት ታሪካዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲታደስ የዲዛይንና የፋይናንስ ድጋፍ ሊያደርግለት ይገባልም ብለዋል። የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅርሱን ለመታደግ ከዚህ በፊት ተጀምሮ የተቋረጠው ጥገና ቅርሱን የባሰ የጎዳው መሆኑን ተመልከተናል ነው ያሉት ሰብሳቢው። ይህም ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጀምሮ እስከ ከተማ መስተዳድር ድረስ ተቀናጅቶ በጥናት ላይ የተደገፈ ስራ ያለመስራት ውጤት ነው ብለዋል። የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም ግንባታ ካለቀ ቆይቷል፤ ነገር ግን እስካሁን ወደ አገልግሎት ያልገባበት ምክንያት ቢብራራ የሚለውንም አንስተዋል በሪፖርታቸው። የአንድራቻ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያንና የቶንጎላ መስጊድ የቅርስ ቦታዎችም አደጋ እንደተጋረጠባቸውና በአስቸኳይ የጥገና ስራ ሊሰራላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው የጎሬ የኢንግሊዝ ቆንሲላ ህንፃ  በጣልያን የኢትዮጵያ ወረራ ጊዜ አፄ ኃይለስላሴ ወደ ኢንግሊዝ ሲሰደዱ በዚሁ ህንፃ አልማዝና ወርቅ ቀብረውበታል በሚል ትርክት ሰዎች ህንፃውን አፈራርሰው አደጋ አድርሰውበታል ብለዋል። ይህን ህንፃውን የማፍረስ አመለካከትም በህብረተሰቡና በአባቢው አመራር በጋራ የማስቆም ስራ ተሰርቷል፤ ከዚህ ባሻገር ባለስልጣኑ የጥገና ዲዛይንና የመነሻ ስራ ፋይናንስ ድጋፍ አድርገናል ድጋፍ ሰጪውንና ከማህበረሰቡ ለማስተባበር እየሰራን ነው ብለዋል። የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት ታሪካዊ ይዘቱን የሚያጠፋ የጥገና ስራው እንዲቆም አድርገናል። የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት የጥገና ስራ በገንዘብ እጥረት ሳይሆን በእንጨት የሚገነቡ ቤቶች ባለሙያዎች እጥረትና የአመራር የቅንጅት አሰራር ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው ብለዋል። በመሆኑም ባለፉት ሶስት ወራት ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ጋራ በመሆን ባለስልጣኑ የዲዛይን ስራ ሰርቶ ሰጥቷል፤ በዓለም ዓቀፍ በእንጨት ቤቶች ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች የማማከር ስራም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። የቦንጋ የቡና ብሔራዊ ሙዝየም ህጋዊ ተቋም የሚያገኝበት የህግ ማእቀፍ ረቂቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ  የአንድራቻ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያንና የቶንጎላ መስጊድ የቅርስ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ጥገና እንዲደረግላቸው ባለስልጣኑ ዲዛይን ሰርቶ ሰጥቷቸዋል ብለዋል። የጥገና ስራውን የመነሻ ስራ ለመጀመር የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍም አድርገናል፤ የተቀረውን የአከባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር እንዲሰራ ጥረት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል አቶ ዮናስ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም