በደቡብ ክልል ከ400 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ሊካሄድ ነው

59
ሀዋሳ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) በተያዘው ዓመት ከ400 ሺህ ሄክተር በሚበልጥ የተጎዳ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚካሄድ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። ክልል አቀፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል። በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ መና እንዳሉት ከ2003 ዓ.ም  ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  የተጎዳ መሬት አገግሞ ለእርሻ ልማት  እንዲውል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በየዓመቱ በአማካይ 4 ሚሊየን ሰዎችን በማሳተፍ የተከናወነው ይሄው ስራ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተጎዳ  መሬትን ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል። የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሀ መጠን በመጨመሩ  በመስኖ የሚለማ መሬት ተስፋፍቶ  ብዛት ያላቸው  አርሶ አደሮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሆኑ  አቶ መለሰ  አብራርተዋል። በተያዘው ዓመትም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች 3 ሺህ 760 ተፋሰሶችን በመለየት 404 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። በንቅናቄ መድረኩ ከደቡብ ክልል ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሴክተር አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም