በየአካባቢው የተከማቹ ቆሻሻዎች ለህጻናት ልጆች ጤና ጠንቅ እየሆኑ ነው

71
አዲስ አበባ  ሰኔ 18/2010 በአዲስ አበባ ከተማ በየአካባቢው ተከማችተው የሚገኙ ቆሻሻዎች ሳይነሱ በመቆየታቸው ለህብረተሰቡ በተለይም ለህጻናት ልጆች ጤና ጠንቅ እየሆኑ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። በከተማዋ ከመኖሪያና ከንግድ ቤቶች እየወጡ የሚከማቹ የደረቅ ቆሻሻዎች ነዋሪው እያማረሩና የጤና ስጋት ላይ እየጣሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የኢዜአ ሪፖርተር በተዘዋወረችባቸው የመዲናዋ የተለያዩ ስፍራዎች ችግሩ መኖሩ ተረጋግጧል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በየስፍራው ተከማችቶ የሚገኘው ቆሻሻ በወቅቱ ባለመነሳቱ የህጻናት መጫወቻ ቦታዎች የጤና ስጋት እየሆኑ መጥተዋል። ቆሻሻው በአግባቡ እየተወገደ ባለመሆኑ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ በጎርፍ እየተወሰዱ የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን የሚዘጉ በመሆናቸው የሚመለከተው አካል ከህብረተሰቡ ጋር በመናበብ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። የክረምቱ ወቅት ህጻናት እረፍት የሚሆኑበት ጊዜ በመሆኑ የጤና ስጋት ተጋላጭነታቸው እንዳይጨምር በተለይም ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተጋላጭ እንዳይሆኑ ቆሻሻ የማስወገድ ስራው በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ከክረምት ጋር ተያይዞ ለሚከሰተው የአተት በሽታ የቆሻሻዎቹ መከመርና አለመነሳት ለህብረተሰቡ ጤና መታወክ አይነተኛ ሚና እንዳላቸውን ተናግረዋል። የከተማው ነዋሪ ወጣት ሄለን ደበበ "ቆሻሾች  ተከምሮ ነው ያሉት የሚያነሳውን የለም አሁን ደግሞ ወቅቱ ክረምት ነው ህጻናት መጫወቻ ቦታ የላቸውም እንደገና ደግሞ ቆሻሻው ጎርፍ ይዞት ሲሄድ ትቦ ይደፈናል ብዙ አደጋ ነው ያለው  " ብለዋል በአስተያየታቸው፡፡ ቆሻሻው ከመኖሪያና ከንግድ ቤቶች ወጥቶ ለቀናት በመቆየቱ የሚያመጣው መጥፎ ጠረን ህብረተሰቡ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። "እንደምታዩት ቆሻሻው ተከምሯል ህጻናት ልጆች የሚጫወቱበት አካባቢ ነው ህጻናቶቹን ለበሽታ ያጋልጣል ፤ቆሻሻው ሽታው ሁሉ አያሳልፍም ቶሎ ቶሎም አይነሳም ስለዚህ የተሻለ ነገር ቢደረግ መልካም ነው" የሚሉት የአዲስ አበባ  ነዋሪ ወይዘሮ አይናለም አለሙ፡፡ የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ ችግሩ መኖሩን አምኖ ለመፍታት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ተናግሯል። አሁን ወቅቱ ክረምት በመሆኑና የአተት በሽታ የሚከሰትበት በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል ብሎም የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በሚያስችል ደረጃ ቆሻሻ ለማንሳት ባለሙያዎች ተመድበው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሩን የመከላከል ሃላፊነት የሁሉም በመሆኑ ህብረተሰቡም ቆሻሻዎችን በመለየት ሊጣሉ በሚገባቸው ቦታዎች ላይ በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል። በቀጣይም ለተመሳሳይ ችግሮች ህብረተሰቡ ተጋላጭ እንዳይሆን በማድረግ ረገድ ኤጀንሲው ከህዝቡ ጋር በመተባባር የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም