ኢትዮጵያና ጂቡቲ በንግድ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

831

አዲስ አበባ ጥር 15/ 2012 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያና ጂቡቲ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

በጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት የዴራል የክልል የስራ ኃላፊዎች ጋር የሞጆ ደረቅ ወደብ የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝቷል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ በጉብኝቱ ወቅት “ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም በደረቅ ወደብ የምታከናውነው የስራ እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በሎጂስቲክ ዘርፍ በጋራ የሚሰሩባቸው የተለያዩ ዘርፎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ”ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የመግቢያ በር ሆና ማገልገሏንም ትቀጥላለች” ብለዋል።

ኢትዮጵያም ባላት የደረቅ ወደብ አማካኝነት የመግቢያ በር ለሌላቸው የምስራቅ አፍሪካ አገሮች አገልግሎት በመስጠት ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር እንዳለባት ጠቁመዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች በደረቅ ወደብ አገልግሎት ለማስተሳሰር እያከናወነ ያለውን ተግባር ከጉብኝቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያና ጂቡቲ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን የቆየ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር የሁለቱን አገሮች ህዝብ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ትብብራቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።

የልዑካን ቡድኑ የተለያዩ አለም ዓቀፍ አምራች ኩባንያዎች የሚገኙበትን የዱከም ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘታቸው ተገልጿል።

ይህም ለጂቡቲ ባለሃብቶችና የምስራቅ አፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት መጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ አሚን ጁንዲ በክልሉ ፕሬዚዳንት የተመራ የልዑካን ቡድን ከወራት በፊት የጂቡቲ የወደብ እንቅስቃሴ ጉብኝትን ተከትሎ የጂቡቲ ልዑክ መምጣቱን አስታውሰዋል።

ከልዑኩ ጋር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የምጣኔ ሃብት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከርና በሌሎች ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር እየመከረ መሆኑን ገልጸዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዋና ዳሬክተር አቶ ደረጀ ሚደቅሳ የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ለማሻሻልና ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከልም የማስፋፊያና ተጨማሪ አገልግሎት አገልግሎት ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ የመግቢያ በር በመሆን እያገለገለች ከምትገኘው ጂቡቲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ምክክሮችን እንደተደረጉም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት የደረቅ ወደብ እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን በመልቲ ሞዳል የሚገባ ኮንቴነር በማስተናገድ የሞጆ ደረቅ ወደብ ቀዳሚ ነው።

ከ11 አመት በፊት የተመሰረተው ይህ ወደብ በወቅቱ ይይዝ ከነበረው አንድ ሺህ ኮንቴነር በአሁኑ ወቅት 30 ሔክታር መሬት በማልማት በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅሙን ወደ 16 ሺህ ኮንቴነር አሳድጓል።

በቀን በአማካኝ እስከ 5 ሺህ ገቢና ወጪ ኮንቴነርን እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትን በውስጡ አካቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።