በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት ውጫዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሊሰራ ይገባል - ምሁራን

67
ጥር 15/ 2012( ኢዜአ) በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ውጫዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ። ዩኒቨርሲቲዎች የሀሳብ መፍለቂያና ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህል የሚታይባቸው መሆን ሲገባቸው በኢትዮጵያ ግን ይህ እየተስተዋለ አይደለም። ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በቀላሉ የሚነሱ ግጭቶች ለተማሪዎች ህልፈት እንዲሁም ትምህርት መቋረጥ ምክንያት እየሆኑ ነው። ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ መንግስት ጥፋተኛ ናቸው ባላቸው ከ400 በላይ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወስዷል። እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም ግን ልብ የሚያደርስ መፍትሄ አለመምጣቱ ለምን? የሚል ጥያቄ ያጭራል። አወት ሀለፎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ የሠላምና ደህንነት ተመራማሪ ናቸው። በተማሪዎች መካከል የሚስተዋለው ግጭት ከካፌ፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ ወይም ከመልካም አስተዳደር ችግሮች በላይ የሚሻገር ነው ይላሉ። "በአገሪቷ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ለዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋት ምክያት ነው" ያሉት አቶ አወት ፖለቲከኞች ለጥያቄና ተቃውሟቸው ዩኒቨርሲቲዎችን የመጫወቻ ሜዳ ማድረጋቸው ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል። በተለይም የማንነትና የብሄር ጉዳዮች ተማሪዎችን ለማነሳሳት ቀላል በመሆናቸው ግጭቶች በቀላሉ እየተከሰቱ መሆኑን ይገልጻሉ። እንደ ተመራማሪው ገለጻ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ የመደማመጥ ባህል ሊጎለብት ይገባል፤ መንግሥትም ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል። የፖለቲካ ዘዋሪዎች ልዩነቶቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች አምጥተው ግጭት ከሚፈጥሩ ይልቅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባም ነው አቶ አወት ያሳሰቡት። ተማሪዎችም ግጭት የሚቀሰቅሱ ውጫዊ ጉዳዮች ሲመጡ በስሜት ከመጓዝ ይልቅ ቆም ብለው በማሰብ በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ መስፍን ማናዜ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋት የፖለቲካው አለመረጋጋት ውጤት ስለመሆኑ ይስማማሉ። ለዚህ ትልቁ መፍትሄ በአገሪቷ የሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን መስማት መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን ልሂቃኑ ያሏቸውን ተቃርኖዎች በሰለጠነ መንገድ መፍታት ሲጀምሩ ችግሮች ይቃለላሉ ባይ ናቸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተማሪዎች አይነኬ በሚባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ በማድረግ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ የመፍታት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል። "በማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚለቀቁ የተጋነኑና ሀሰተኛ መረጃዎች ችግሩን እያባባሱት ነው" ያሉት መምህሩ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አክለዋል።                                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም