የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክት በሚቀጥለው ግንቦት ወር የሙከራ ምርት ይጀምራል ተባለ

62
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክት በቀጣዩ ግንቦት ወር የሙከራ ምርት ማምረት እንዲጀምር እየተሰራ መሆኑን ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ ያለበትን የግንባታ ሁኔታ አስጎብኝቷል። ፕሮጀክቱ በ2004 ዓ.ም በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ (ሜቴክ) በ235 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በ18 ወራት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ስራውን መጀመሩ ይታወቃል። ሆኖም የፕሮጀክቱ ግንባታ እስከ 2010 ዓ.ም ሲጓተት ቆይቶ ለፋብሪካው ግብአት የተተከለው ሸንኮራ አገዳም በተደጋጋሚ እየተወገደ ለኪሳራ ሲዳርግ ቆይቷል። ከሜቴክ ጋር የነበረው የግንባታ ውል እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ አፈፃፀሙ 65 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን 257 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብርም ወጭ ሆኗል። ፕሮጀክቱ የዲዛይን፣ የጥራትና የአተካከል ሚዛን መዛባትና ሌሎች ችግሮችም ተስተውለውበታል። በመሆኑም ከሜቴክ ጋር የነበረው ውል ተሰርዞ በ2011 ዓ.ም ከቻይናው ሲኤምሲ ኢንጂነሪንግ ጋር በ95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የግንባታ ስምምነት ውል ተፈፅሟል። በዚህም ከባለፈው መስከረም ጀምሮ በአዲስ መልክ የማስተካከያ ስራ በመሰረት ላይ ይገኛል። በቀጣዩ ግንቦት ወር ፋብሪካው የምርት ሙከራ ለማስጀመር የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዩ ሮባ ተናግረዋል። የግንባታው መጓተት በ13 ሺህ 147 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው የሸንኮር አገዳ ምርት ለተከታታይ ዓመታት ባክኗል። አሁን ላይ ለፋብሪካው የሸንኮራ ምርት በ2 ሺህ 352 ሄክታር ማሳ ላይ ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ቀጣይም የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ አሰጌ እንደገለፁት ከሆነ በ6 ሺይ ሄክታር መሬት ላይ ለምቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ምርት በማርጀቱ ተወግዶ በአዲስ ምርት እየተተካ ነው። በቻይናው ሲኤምሲ ኢንጂነሪንግ ኮባንያ የፕሮጀክቱ ግንባታ ማናጀር ሚስተር ጃክ ዣንግ በበኩላቸው በቀጣዩ ግንቦት ላይ የሙከራ ምርት ለማስጀመር የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል። ሆኖም የግንባታ እቃ አቅርቦት፣ የባለሙያዎች አለመሟላትና መሰል ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ሂደት እገዛ እንደሚያደርግልን በመተማመን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፀፋሚ አቶ ወዩ ሮባ እንደሚሉት ለግንባታው መጓተት ምክንያት ሆነው የተለዩ ችግሮች እንድፈቱ በመንግስት በኩል አቅጣጫ ተቀምጧል። የጣና በለስ ቁጥር አንድ እና ሁለት የስኳር ፕሮጀክቶች ግንባታ የተጀመረው በ2004 ዓ.ም ነበር። ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ብቻ የፕሮጀክቱ መጓተት የ7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስከተሉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም