የመጠጥ ውሃና መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መጓተትን ለመቀነስ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ይሰራል

107
አዲስ አበባ ጥር 15 / 2012 (ኢዜአ) የመጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክቶችን ግንባታ መጓተት ለመቀነስ የግሉን ዘርፍ በትላልቅ ፕሮጀክቶች በማሳተፍ እንደሚሰራ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። የአሰራር፣ የተቋራጮችና አማካሪዎችን አቅም ከማሳደግ ባሻገር ችግሮችን ለመፍታትም ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ይሰራል ብሏል። ሚኒስቴሩ ይህን ያለው ከግሉ ዘርፍና ከክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶችና አጋር ድርጅቶች ጋር እያካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ነው። የግሉን ዘርፍ የወከሉት አቶ ጌታሁን ታገሰ በዘርፉ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች ሁለት አስርት ዓመታትና ከዛ ያነሰ የምስረታ ጊዜ ያስቆጠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። በእነዚህ ጊዜያት የመንግስትን አቅጣጫና ፖሊሲ በመከተል 'በዘርፉ አስተዋፅኦ ስናደርግ ቆይተናል' ያሉት አቶ ጌታሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረገው ለውጥ ከውጭ በሚያስመጡት እቃ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል። መድረኩ በድክመትና ተግዳሮቶች ላይ ለመነጋገር እድል የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለአገር በቀል ተቋራጮች እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በምክክር መድረኩ እንደተገለፀው በአገሪቷ እየተሰሩ ያሉ የመስኖም ሆነ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መጓተት ሳቢያ የሚገነቡበት በጀት በእጥፍና ከዛም በላይ እያደገ ነው። በአገሪቷ የመጠጥ ውሃና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ቢሆንም ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር ቀሪ ስራ አለ ያሉት ደግሞ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ናቸው። በዘርፎቹ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ጥራታቸውን እንዲጠብቁና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሚኒስቴሩ በሶስት ዘርፎች በመደራጀት መመራት መጀመሩን አንስተዋል። የመጠጥ ውሃ፣ መስኖና ተፋሰስ ልማት ዘርፎችን ከዳይሬክቶሬት ወደ ኮሚሽንና ባለስልጣን ደረጃ ከማሳደግና መምራት ባሻገር ዘርፉን የግሉ ዘርፍ እንዲመራው እንደሚደረግም ነው የጠቆሙት። የግሉ ዘርፍ ከዚህ ቀደም በኃይል ዘርፍ ተሰማርቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አውስተው በቀጣይም በመጠጥ ውሃና መስኖ ዘርፍ የሚከወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አገር በቀል ተቋራጮች እንዲይዙና በኮንትራትም ሆነ በዘላቂነት እንዲያስተዳድሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የተቋራጮችና አማካሪዎችን አቅም ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን ለመፍታትና የግንባታ መሳሪያዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ለማድረግም በጋራ ይሰራል ብለዋል። ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል። እስከ ነገ የሚዘልቀው መድረክ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በመስኖ ልማት ዙሪያ ይመክራል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም