''ማርጯ''ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ተመሰረተ

168

ሶዶ ጥር 15 / 2012 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ''ማርጯ''የተሰኘ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ተመሰረተ።

በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ''ማርጯ''የተሰኘ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ተመሰረተ።

አክሲዮን ማህበር መስራች ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ሐብታሙ ጢሞቴዎስ በዚሁ ወቅት አክሲዮን ማህበሩ ብድር አቅርቦትንና ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ ሥራ መፍጠርና ቁጠባን የማሳደግ ዓላማዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም 22 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አክሲዮን መሸጡንና 500 አባላት እንዳፈራ አስታውቀዋል።

አቅም ኖሯቸዉ በመነሻ ካፒታል እጥረት የሚቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የማምረቻ ድርጅቶችን ብድር በማቅረብ በድህነት ቅነሳው ጥረት ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ራሱን ወደ ባንክነት ለማሳደግና ወደ ሌሎች አገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፍ ለመክፈት ራዕይ እንዳለው ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።

አክስዮን ማህበሩ ወደስራ ሲገባ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የደንበኞቹን ቁጥር 50 ሺህ ለማድረስ ዕቅድ ይዟል ብለዋል።

በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ቅርንጫፎች እንደሚከፍትና ከ350 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ እንደሚፈጥርም  አቶ ሐብታሙ ተናግረዋል።

በአራት ልጆቻቸው ስም የ400 ሺህ ብር አክሲዮን የገዙት አቶ አምሳሉ መሰኔ ተቋሙ በሚያቀርበዉ የብድር አቅርቦት ከሚፈጥረው ዕድል ባሻገር፤ ትርፋማ እንደሚያደርግ በማሰብ አክሲዮን መግዛታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክሲዮኑ በዘላቂነትና በረጂም ጊዜ ቆይታ ከሚያስገኘው ትርፍ በመጠቀም ልጆቻቸው ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ አስበው መግዛታቸውን በመጠቆም፡፡

አቶ ሚልኪያስ አንጁሎ ለመጀመሪያ ዙር የግማሽ ሚሊዮን ብር አክሲዮን መግዛታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ አክሲዮን ማህበሩ ልማት ለማፋጠን ዉጤታማና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

ሥራ አጥነትን ለማስወገድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

''ማርጯ''የመጀመሪያው የወላይታ ሥርወ ነገሥታት መገበያያ ገንዘብ እንደነበርም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም