ምክር ቤቱ የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ወሰነ

68
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ወሰነ። ከዚህ ቀደም በከተማው ካቢኔ የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ረቂቅ ሀሳብ ያዘጋጀ ሲሆን የከተማዋ ምክር ቤትም ኤጀንሲው እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል። የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የተማሪዎች ምገባ ፣ የትምህርት ግብዓት አቅርቦት እና የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦት ቀጣይነት የሚኖረውና በኤጀንሲው የሚመራ ይሆናል።
ኤጄንሲው ተጠሪነቱ ለከተማው ከንቲባ ሲሆን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተውጣጣ ቦርድ የሚመራም እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ቦርዱ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትና ወጣት ተማሪዎች በምግብና በትምህርት ግብዓት አቅርቦት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ በቋሚነት የሚሰራመሆኑም ተጠቅሷል። በተያዘው የትምህርት ዘመን በከተማ አስተደዳሩ አነሳሽነት ለ600ሺህ ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ደብተርና የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከ300ሺህ በላይ ታዳጊ ተማሪዎች ደግሞ የምገባ መርሀ ግብር ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ለተማሪዎች የሚደረገው ድጋፍ በብዛትና በጥራት የተሻለ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራ ኢ/ር ታከለ ኡማ መናገራቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም