የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከደቡብ ወሎ አመራሮች ጋር እየተወያዩ ነው

75
ደሴ፤ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ዙሪያ ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በደሴ ከተማ እየተወያዩ ነው። በውይይቱ የፌዴራልና የአማራ ክልል አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓሊ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት ውይይቱ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችና ጥንካሬዎችን መሠረት ያደረገ ነው። በተለይም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት የበጋ ወቅት ሥራዎች  ውጤታማነት እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። በነገው ዕለትም የዘንድሮውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከማስጀመር ጋር ተያይዞም የተሻለ መግባባት ለመድረስ  እንደሚረዳ አቶ ዓሊ ገልጸዋል። በዞኑ በበጋ ወቅት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከ610 ሺህ በላይ ሕዝብ  ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ውስጥ ሥራውን ያከናውናል ብለዋል። በሥራው ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ በዚህም የደን ሽፋኑን አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ 14 በመቶ  ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። በዚሁ ውይይቱ በ24 ወረዳዎች የተውጣጡ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል። ሚኒስትሩ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ቀጣይ አቅጣጫ ያመላክታሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዞኑ የዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በደሴ ዙሪያ ይጀመራል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም