ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

116

አዳማ፤ ጥር 15/ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ።

ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለኢዜአ  እንደገለጹት ዕቃዎቹ የተያዙት በአገሪቱ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ላይ በተካሄደ ጸረ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ነው።

በአገሪቷ በተለያዩ መግቢያና መውጫ በሮች በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎች ላይ በተደረገው ቁጥጥር ከተያዙት እቃዎች መካከል ልባሽ ጨርቅ፣ አዳዲስ አልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

ጊዜ ያለፈበት መድኃኒት፣ አደንዛዥ ዕጾች፣የመለዋወጫ እቃዎች፣ የምግብ ሸቀጣሸቀጦችም  ሌሎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዕቃዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ በኤርፖርት በተደረገ ቁጥጥር  የውጭ ገንዘብ ተይዟል ብለዋል።

በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎችና በሌሎችም አካባቢዎች ሲጓዙ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የጸጥታና ከሌሎችም አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አመልክተዋል።

እንዲሁም 230 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የማዕድን ምርቶችና የቁም እንስሳትን ወደ ከአገር ለማስወጣት ሲሞከር ድንበር  መያዛቸውን አቶ ደበሌ ተናግረዋል።

በሥራው ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ቢመዘገብም፤ አሁንም እንቅስቃሴው ከፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በቀጣይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በአገሪቷ አጠቃላይ ከ90 በላይ ኬላዎችን በመክፈት የቁጥጥር ሥራውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም