ለኦሎምፒክ ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚታደሙበት ቴሌቶን ሊካሄድ ነው

141
አዲስ አበባ ጥር 15/2012 (ኢዜአ)  እ.አ.አ ሐምሌ 2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚገኙበት ቴሌቶን እንደሚዘጋጅ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳትፎ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል። የኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት ለቶኪዮ ውድድር ቀድሞ ከነበረው በተለየ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ዝግጅቱን የተሟላ ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር የገቢ ማሳባሰብ ስራ ይሰራል ብለዋል። በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የሚመራ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ መዋቀሩንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚገኙበት ቴሌቶን እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል። የመንግስት የልማት ድርጅቶችና ባንኮች በኦሎምፒክ ውድድሩ አሻራቸውን ያሳርፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ባለሀብቶች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናከረው እንዲሚቀጥሉም ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለሚያሸንፉ አትሌቶች ከከዚህ ቀደሙ የላቀና ዳጎስ ያለ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚኖር ዶክተር አሸብር ገልጸዋል። ይህንን አገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት የመገናኛ ብዙሃን አትሌቶችን ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በማበረታታት ለሚጠበቀው ድል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል። በቶኪዮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት ትጠብቃለች። በተጨማሪም በኦሎምፒኩ በቴኳንዶ፣ በቦክስና በውሃ ዋና ውድድር ለመካፈል በማጣሪያ ውድድሮች ላይ እንደምትሳተፍ ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም