የግል ድርጅቶች የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ማክበር እንደሚገባ ተመለከተ

68

ጋምቤላ፤ ጥር 15/ 2012( ኢዜአ) የግል ድርጅቶች የሠራተኞችን መብትና ጥቅም በማክበር የኢንዱስትሪውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በጋምቤላ ክልል የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በከተማዋ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር በሰራተኞች አያያዝና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡

የኤጀንሲው የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ተስፋዬ በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት የኢንዱስትሪውን ሰላምና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ባለሀብቶች የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡

ባለሀብቱ በተለይም ለሰራተኛው ከሚከፍለው ደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች በተጨማሪ የተቀጣሪውን የጡረታ ዋስትናንም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ማስጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በክልሉ የሚገኙ የግል ሰራተኞችን መብት ለማስከበርና ጥቅማቸውንም ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተለይም በክልሉ በኮንስትራክሽን፣በሆቴል፣በበጎ አድራጎትና በሌሎችም መስኮች የተሰማሩ ድርጅት ሰራተኞችን ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ መመዝገቡንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረጉን አቶ ታሪኩ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞችን የጡረታ ዋስትና እንዲጠበቅላቸው አድርጓል ብለዋል።በቀጣይም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ለዚህም ስኬታማነት አሰሪው፣ሠራተኛውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከተገኙት ባለሀብቶች መካከል አቶ ታሪኩ አበራ በሰጡት አስተያየት ውይይቱ የሠራተኛውን መብት ለማስከበርና ሠራተኛው ተረጋግቶ  የሚሰራበትን ሁኔታ ለመፍጠር  እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

አንድ ሠራተኛ ቋሚ ተቀጣሪ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ሙሉ የጡረታ ዋስትናው እንዲጠበቅለት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ በላቸው ሞላ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሠራተኛው ከመንግሥት መስሪያ ቤት ለቆ በድርጅቱ ቅጥር በሚፈጽምበት ጊዜ የጡረታ ዋስትና መለያ ቁጥር ባለመያዛቸው እንደ አዲስ የሚመዘገቡበት ሁኔታ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከመንግስት መስሪያ ቤት በመልቀቅ ወደ ግል ድርጅቶች የሚመጡ ሠራተኞችን የማህበራዊ ዋስትና ለማስጠበቅ በጋራ እየተሰራ መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም