ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር እንዲተዳደሩ ተወሰነ

64

አዲስ አበባ፤ (ኢዜአ) ጥር 14/2012 በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር ይተዳደሩ የነበሩ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዘዋወሩ ተወሰነ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 78ኛ መደበኛ ስብሰባው በስድስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው።

በአገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተጀመረው የሪፎርም ስራዎች አንድ አካል የሆነውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 መሰረት ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን ቀደም ሲል ከነበሩበት ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡

በዚሁ መሰረት የደጀን አቪዬሽን ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሚውኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና የፊውል ነዳጅና ፕሮፒላንት ንዑስ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በአንድ ኮርፖሬሽን ስር በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ይቻል ዘንድ የመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ ካያቸው አጀንዳዎች መካከል የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ የምርምርና የልማት ማዕከል ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው።

አገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በምርምር፣ ልማትና ትግበራ የተመሰረቱ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ አገልግሎቶች፣ ምርቶችና መፍትሄዎችን መስጠትና የልህቀት ማዕከል ማቋቋም በማስፈለጉና በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዙሪያ ላይ ለሚሰሩ ጀማሪ አልሚዎች ምቹ ምህዳር መፍጠር የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ቀርቧል።

በዚህም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀባይነት ስላገኘ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

ምክር ቤቱ ሌላ የተወያየበት አጀንዳ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ህጋዊ ሰውነት እንዲሰጠው በሙሉ ድምጽ በመወሰን ረቂቅ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

የሲቪል አቪዬሽን አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ ሌላው በምክር ቤቱ የታየ ጉዳይ ሲሆን ነባሩ የማስፈጸሚያ አዋጅ በቆየባቸው የትግበራ ዓመታት ውስጥ በህግ ያልተሸፈኑ አዳዲስ አስተሳሰቦች እና የቁጥጥር ስርአቶች መኖራቸውን ተመልክቷል።

በመሆኑም የሰው ሀብት ስምሪትና የተፈላጊ ብቃት ተለዋዋጭነት መኖሩ በተለይም ከዘርፉ ልዩ የስራ ባህሪ አንጻር የአቬዬሽን ዘርፉን ለመምራትና ለመቆጣጠር፣ የበረራ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ አለም ዓቀፍ ድርጅቱ በየጊዜው የሚያወጣቸው ምክረ ሀሳቦች፣ ደረጃዎችና የተመረጡ አሰራሮች ተግባራዊነት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ክፍቶቶችን በሚሞላና የወደፊት የኢንዱስትሪውን እድገት በጠበቀ መልኩ ለመደገፍ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ አስተላልፏል።

አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ  ምክር ቤቱ የተወያበት ሌላኛው አጀንዳ ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ጊዜው የሚጠይቀውንና ደረጃውን የጠበቀ የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረካ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የፍትህ ስርአት ለመገንባት የተፈጸሙ ወንጀሎችን መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ ለወንጀል መነሻ ምክንያቶችን በመቀነስ ወይም በማጥፋት ጭምር ለመስራት የሚያስችል አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ የጠቅላይ አቃቤ ህግ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ስትራቴጂው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ስትራቴጂው በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተመለከተው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡

በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

የአካባቢ መራቆትንና የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን በመከላከል፣ የውሃ ሀብትን በማጎልበትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ የመሬት የማምረት አቅም ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍና በዚህም ለእርሻ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ መደላድል ለመፍጠር እንዲቻል ቀደም ሲል የተጀመሩትን የተፋሰስ ልማት ስራዎች ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም