በምእራብ ጉጂ ዞን ገላና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ተጀመረ

132
ነገሌ ኢዜአ ጥር 14 ቀን 2012  በምእራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት ለአንድ ወር የሚቆይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ። በተያዘው የበጋ ወራት አካባቢያቸውን ለማልማት በመስራት ላይ መሆናቸውን   የወረዳው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የወረዳው ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ታምሩ እንዳሉት 37 ሺህ በላይ የወረዳው ነዋሪዎች የተካፈሉበት ሥራ በመካሄድ ላይ ነው። በሥራው 8 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የሚለሙ 17 ተፋሰሶች መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡ በሥራው መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ መከለል፣ ችግኝ ማዘጋጀት፣ የድንጋይና የአፈር እርከን መስራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ባለፈው ዓመት በ2ሺ 576 ሄክታር መሬት ላይ ከተተከለው 8 ሚሊዮን ችግኞች 88 በመቶ መጽደቁን አስታውሰዋል፡፡ በወረዳው የቀርሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሚራ በቀቴ ባለፉት  ዓመታት በተከናወኑ   ተራቁተው የነበሩ አረንጓዴ መልክ መያዛቸውን አስታውሰዋል፡፡ በቀዳሚዎቹ ዓመታት ባከናወኑት ሥራ የመጠጥ ውሃ ለማግኘትና የእንስሳት መኖ ለማልማት መቻላቸውን ገልጸዋል።ይህም ለአሁኑ ሥራ መነሳሳት ፈጥሮብኛል ብለዋል። በሳምንት ሦስት ቀን እርከን መስራትና ችግኞችን በመትከል በሥራው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡ ደንጎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅነሽ ገመዴ የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ጊዜ የማይሰጠው የህልውና ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። ሥራውንም በማንም ትእዛዝና ቅስቀሳ ሳይሆን፤ በራሴ ፍላጎትና ተነሳሽነት  እየተሳተፍኩ ነው ብለዋል፡፡ ሥራው ካለፈው ዓመት bሚለማው መሬት  በ2 ሺህ ሄክታር መሬት በሰው ኃይል ደግሞ 3 ሺ 800 ብልጫ እንደታየ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም