በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የሚታዩ የቅንጅት ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ አልተፈቱም- ኤጄንሲው

113
አዳማ ጥር 14 / 2012 (ኢዜአ)  በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የሚታዩ የቅንጅት ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተፈቱ የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጄንሲ ገለጸ። ኤጄንሲው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ኢትዮ ቴሌኮም፣የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣መንገዶች ባለስልጣንና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት ጋር የግማሽ ዓመት የጋራ እቅድ አፈፃፀም በቢሾፍቱ ከተማ በመገምገም ላይ ነው። የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አልማው መንግሥት በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ለኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ዝርጋታ የሚታዩ ችግሮች አልተቃለሉም። የተቋማቱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ችግር የሕዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ከመቀጠላቸውም ባለፈ ተገቢውን ምላሽ አላገኙም ብለዋል። ኤጀንሲው ችግሮቹን ከመሠረታቸው ለማስወገድ  ባደረገው ክትትል የፕሮጀክቶች ጥራት ጉድለት፣የቅንጅትና መናበብ ክፍተት፣አንዱ በአንዱ ላይ ማነቆ መሆንና አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። በተለይ የወሰን ማስከበርና ካሳ ክፍያ፣በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ የተለያየ ካሳ መጠየቅ፣ የተደጋጋመ የዲዛይን ጥናት፣ከክልል መንግስታት ለፌዴራል ፕሮጄክቶች የሚደረገው ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆን በዘርፉ የተለዩ ማነቆዎች መሆናቸውን አመልክተዋል። ኤጄንሲው ከተቋማቱ ጋር በመቀናጀት በፌዴራል ደረጃ ከሚተገበሩት የልማት ፕሮጄክቶች ውስጥ የከፋ ችግር ያለባቸውን 80 ፕሮጄክቶች በጥናት በመለየት የጋራ የተቀናጀ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መግባቱንም ገልጠዋል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የ34 ፕሮጀክቶችን ችግር በመፍታት የግንባታ ሂደታቸው የተቋረጠው እንዲቀጥል አድርገናል ያሉት አቶ አልማው፣ የሞጆ ሐዋሳ ፍጥነት መንገድ፣የአዳማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣የቦሌ አቦምሳ የአስፋልት መንገድን በአብነት ጠቅሰዋል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ የጋራ የሆነ የተናበበ እቅድ ስላልነበራቸው በሚያከናውኑት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የመጠላለፍ አባዜ ነበረባቸው ያሉት ደግሞ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰዒዳ ከድር ናቸው። ባለፉት ስድስት ወራት ተቋማቱ የጋራ እቅድ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ በክንውን ላይ የሚኖረውን ከፍተት በድጋፍና ክትትል በመሙላት የተሻለ አፈፃፀም ማስዘገባቸውን ተናግረዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ኢትዮ ቴሌኮም፣የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣መንገዶች ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የጋራ የተናበበ እቅድ አዘጋጅተው ወደ ትግበራ መግባታቸውን አስታውቀዋል። በሪፖርቶች ላይ ክፍተት መኖሩን  ያመኑት ወይዘሮ ሰዒዳ፣ በቀጣይ ስድስት ወራት 50 የከፋ ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዕቅዳችን በመከለስ ላይ እንገኛለን ብለዋል። የኤጀንሲው የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ቡድን መሪ አቶ ቴዎድሮስ አበበ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከቱት ተቋማቱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ተናበውና ተቀናጅተው እንዲያከናውኑ የጋራ ግንዛቤና አቅም ተፈጥሯል። በቅንጅት ሥራ በተናጥል ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ በጥራትና በአፈፃፀም ሁሉንም መሠረተ ልማት የዳሰሰ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል። በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ አግባብ ካላቸው ተቋማት የተውጣጡ  አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም