ባለፉት ስድስት ወራት ከ127 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

72
አዳማ፤ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) በዘንድሮው ግማሽ የበጀት ዓመት ከ127 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ የስድስት ወራት  እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው። የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ  ከግምገማው ጎን ለጎን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ሚኒስቴሩ በግማሽ በጀት ዓመቱ የሰበሰበው ገቢ በእቅድ ከያዘው በአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 29 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል። ይህም የአገሪቱ የገቢ አሰባሰብ ጥሩ መሻሻል ማሳየቱን ያመለከቱት ሚኒስትሯ፣ አብዛኛው ገቢ የተሰበሰበው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ መሆኑን ገልጸዋል። ከገቢው 58 በመቶ ከአገር ውስጥ  የተሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪው ከጉምሩክ፣ ቀረጥና  ታክስ የተሰበሰበ ነው ብለዋል። ከአሁን በፊት ሚኒስቴሩ ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ጋር የነበረው ግንኙነት በመካሰስ ላይ የተመሰረተ ስለነበር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተባብሮ ለማሳደግ ያላስቻለ ነበር ብለዋል። ይህንን ለመቀየር አሠራርን ከማዘመን ጀምሮ አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ለተገልጋይ የተሻለ መስተንግዶ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ በመደረጉ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ግብር ከፋዩ ከፍተኛ የባህሪ መሻሻል በማሳየቱ ግብሩን በወቅቱ አሳውቆ የሚከፍልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት። በቀጣይም የአሰራር ማሻሻያ ስራዎቻችንን ቀጣይነት በማረጋገጥ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 268 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚደረግ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም