በሰው የመነገድና ሕገ ወጥ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

106
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ። ምክር ቤቱ በዛሬው 10ኛ መደበኛ ስብሰባው በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል። በሰው የመነገድ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ለስራ ወደ ውጭ አገር የመላክ ወንጀል በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጿል። የፀደቀው አዋጅ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የአካል፣ የህይወትና የደህንነት እዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መከላከል እንደሚያስችል ተገልጿል። ወንጀሉን ለመከላከል፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ፣ ለተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም እንደሚረዳም ነው የተነገረው። በተለይም ለወንጀሉ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግና የተጎጂዎችን ዕድሜ፣ ጾታና ልዩ ፍላጎት ያማከለ ስራ ለመስራትና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችልም ተጠቅሷል። ረቂቅ አዋጁ በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ድርጊትና ወንጀል የሚከላከሉ የሕግ ማዕቀፎች የተበታተኑ በመሆናቸው በአፈፃፀም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያስችል ሁኔታ ወደ አንድ እንዲሰባሰቡ አድርጓል። ረቂቅ አዋጁን የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴና የሴቶች ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው በጋራ ያቀረቡት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም