ከዘንድሮ የመኸር እርሻ 329 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

84
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 በመላው አገሪቱ በዘንድሮ የመኸር እርሻ በሰብል ከተሸፈነው አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ እንዳለው ዘንድሮ 329 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል። በምርት ዘመኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ከመኸር እርሻ 382 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል ። ከዚህ ውስጥ የማዕከላዊ እስታስቲክስ ኤጀንሲ  ባወጣው መረጃ በመኸር ከተዘራው 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 329 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል። ይህም ከባለፈው ዓመት የ4 ነጥብ 33 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ገርማሜ ጋሩማ እንዳሉት በዘንድሮው የመኸር እርሻ አብዛኛው ምርት ተሰብስቧል። የተሰበሰበው ምርት ከሌሎች ዓመታት አንጻር ሲታይ የተሻለ  መሆኑን ጠቁመዋል። በምርት ዘመኑ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የአንበጣ መንጋ ለተዘራው ሰብል ትልቅ ስጋት እንደነበረ ገልጸዋል። እነዚህ ስጋቶች በምርት ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስ የተደረገው ጥረት ስኬታማ እንደነበረ አቶ   ገርማሜ ተናግረዋል። በዘርና በማዳበሪያ አቅርቦትም  ከሌሎች ጊዚያት በተሻለ በወቅቱና በጥራት ለማድረስ ጥረት የተደረገበት ጊዜ መሆኑን በማከል። አስቀድሞ የተደረገው ዝግጅትና የተዘረጋው ቅንጅታዊ አሰራር አገሪቱ በመኸር እርሻ የተሻለ ምርት እንድታገኝ አስችሏታልም ብለዋል። የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ በቀጣዮቹ አስር ቀናት ለቀሪ ምርቶች መሰብሰቢያ የተሻለ የአየር ንብረት እንዳለ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም