ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር መስተማር ስራውን ያወኩ 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

123
ባህርዳር ጥር 14/2012 (ኢዜአ) የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን ሆን ብለው በማወክ የተለዩና ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው 21 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተጀምሯል። የኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ ለኢዜአ እንደገለፁት ሙሉ በሙሉ የታገዱት አራት ተማሪዎችን ጨምሮ ትምህርት እንዲስተጓጎል ያደረጉ 21 ተማሪዎች ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላትም በመለየትና በማጣራት በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። የዩኒቨርስቲ ምሁራን ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ተማሪዎችን በስነ ምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ባለፉት ሳምንታት ተማሪዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ቢደረግም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በፖሊ ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፣ ፔዳና ይባብ ካምፓሶች ትምህርት ተቋርጦ እንደነበረ ተናግረዋል። ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትምህርት ያልተቋረጠበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ፋሽንና ዲዛይን እንዲሁም ግብርና ኮሌጅ በከፊል የተቋረጠባቸው እንደነበሩም አስታውሰዋል። “በውጫዊ ምክንያት ጊቢ ለቀው የወጡ ተማሪዎችም ከጥር 5 እስከ 7/2012 እንዲመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በወሰነው መሰረት ተመልሰው ወደ መማር ማስተማር ገብተዋል” ያሉት ዶክተር ዘውዱ ካለፈው ማከሰኞ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የማስተማር ስራው መቀጠሉን አስታውቀዋል። ትምህርት ተቋርጦ በነበረበት ወቅት የባከነውን ጊዜ ለማካካስ መምህራን ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በትርፍ ሰዓታቸው እንዲያስተምሩ ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል። በዩኒቨርሲቲው የጋርመንት ኢንጂነሪንግ ተማሪና የተማሪዎች ህብረት ፀሐፊ ታምራለች ውቤ በበኩሏ ተማሪዎች መማር ማስተማሩን አቋርጠው ከግቢ የወጡት በአሉባልታ ወሬ ተረብሸው ነው ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ የተፈጠረ ችግር ሳይኖር በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች መቋረጡ ተገቢ እንዳልሆነ አመልክታ፤ “አሁን ላይ ተመልሶ መጀመሩም መልካም ነው” ብላለች። “ትምህርት መማር መጀመሪያ የሚጠቅመው እራስን ነው” ያለችው ተማሪ ታምራለች ከዚያም ቤተሰብንና ሃገርን በመሆኑ ዋጋ ሰጥቶ መማር ይገባል ስትልም ገልፃለች። ተማሪ ማለት ለማን ብሎ መማር እንዳለበት የሚያውቅ መሆን አለበት ያለችው ደግሞ የዩኒቨርስቲው ፋሽንና ዲዛይን ተማሪ ሃና ታደለ ነች። ተማሪው ጠንቅቆ በመማርም እራስን፣ ሃገርንና ቤተሰብን የመጥቀም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ከአሉባልታ ወሬ ወጥቶ ትምህርቱ ላይ ማተኮር እንዳለበት ተናግራለች። የባህርዳርና አካበቢው ህዝብም ተማሪዎችን እንደራሱ ልጆች በመንከባከብ እያሳየው ላለው ቤተሰባዊ ፍቅር አመስግናለች። የባህርዳር ዩኒቨርስቲ በመደበኛው የመማር ማስተማር ፕሮግራም ከ24 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም