በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

69
ደሴ  ጥር 14/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ በቀደማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት 21 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጭ የተገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጠናቀቁን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይማም ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በማህበረሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው። የነበረውን ችግር ለመቅረፍም ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ 21 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ የትምህርት ቤቱን ግንባታ በማስጀመር በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ በታቀደው መሰረት መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ግንባታውን በጥራትና ፍጥነት ለማከናወንም እራሳቸው ወይዘሮ ዝናሽ በየጊዜው እየመጡ ክትትል ማድረጋቸውና ህብረተሰቡም ቀና ትብብሩን በማሳየቱ ነው ብለዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ 19 የመማሪያና ለሌላ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። የትምህርት ቤቱ መገንባትም ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ሳልመኒና ሃርቡ ከተማ ረጅም ርቀት ተጉዘው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችን ችግር እንደሚቀርፍ ታምኖበታል። በቀጣዩ መስከረም ወር ትምህርት ለማስጀመርና ለመማር ማስተማሩ ስራ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ ከክልልና ከዞን መስተዳድሮች ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በአልቡኮ ወረዳ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ አሊ እንደጹት በአቅራቢያቸወው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቻቸውን ደሴና ኮምቦልቻ በመላክ ከፍተኛ ወጭ ለማውጣት ይገደድ ነበር። "እኔም ስምንት ልጆቼን ለማስተማር ቤት ተከራይቼና ስንቅ በማመላለስ ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ስዳረግ ነው የኖርኩት" በማለት ጠቁመው፣ አሁን ላይ ችግሩ በመፈታቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሌላዉ የ013 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሐሰን መሃመድ በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የአቅመ ደካማ ልጆች እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ተምረው ያቋርጡ እንደነበር አውስተዋል። እርሳቸውም እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረው በ2003 ዓ.ም በችግር ምክንያት ማቋረጣቸውን አውስተው አሁን ግን የመማር እድሉ ወደ አቅራቢያቸው በመምጣቱ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት በጎንደር አዘዞ፣ ደባርቅ፣ ሰቆጣና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም