የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጥቃቱን አወገዙ

84
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 መንግስት በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የቦምብ ጥቃት ያደረሱ አካላትን ማንነት በአስቸኳይ አጣርቶ ለህዝብ እንዲያሳውቅና እርምጃ እንዲወስድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጠየቁ። አባላቱ ጥቃቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የተሰነዘረ የሽብር ተግባር ነው ሲሉ ያወገዙ ሲሆን ህይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ዜጎች የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል። ሰልፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በህዝቡ ውስጥ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያሳዩትን ቁርጠኝነትና ተግባር በይፋ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል። በመስቀል አደባባይ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት፣ በደቡብ ክልልና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ግጭቶች የአገሪቱንና የህዝቡን ለውጥ የማይፈልጉ አፍራሽ ኃይሎች ተግባር ነው ሲሉም አውግዘዋል። በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በተመለከተ በህዝቡ ውስጥ ብዥታና ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠር ለመከላከል እንዲቻል በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝቡ ይፋ እንዲሆንና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸው የለውጥ ተግባራትና ሃሳቦች ለአፍሪካዊያንም ጭምር የሚተርፍ በመሆኑ በጋራ እንደሚሰሩና እንደሚደግፉትም ተናግረዋል። የሽብር ተግባሩ በተፈጠረበት ጊዜ ከፀጥታ ኃይሉ በላይ ህዝቡ ከፍተኛውን የማረጋጋትና ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ተግባር ማከናወናቸው የሚበረታታና ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል። ድርጊቱ በቀጣይም እንዳይፈጠርና ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ሰላምን የመጠበቅ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። በመግለጫው አዲስ ትውልድ፣ የወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት፣ የመላው ኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተሳትፈውበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም