ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሠላም በማረጋገጥ አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ትሰራለች

48
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 14/2012 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሠላም በማረጋገጥ አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል። በዳቮሱ የዓለም  ኢኮኖሚ ፎረም የሶስተኛ ቀን ውሎ "የአፍሪካ ሠላም ግንባታ" በሚል ርዕስ የአፍሪካ መሪዎችን በአንድ መድረክ ያሰባሰበ የገፅ~ለገፅ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ "ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሠላም በማረጋገጥ  ጠንካራ አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ጥረቷን ትቀጥላለች" ብለዋል። በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ሠላማዊ ድባብ እንዲሰፍንና የተረጋጋ የኢኮኖሚ መስተጋብር እንዲፈጠር በኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡንም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ የሚገዳደሩ ፈተናዎችን  ለመሻገርና አስተማማኝ ሠላም ለመገንባት ፅኑ አቋም እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። በመድረኩ የታደሙት የአፍሪካ አገራት መሪዎች በሰጡት አስተያየትም የአህጉሪቱን ዘላቂ ሠላም የማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የማጥበቅ አጀንዳ ወቅታዊ ምላሽ የሚሻ መሆኑን አስምረውበታል። አፍሪካ ከሌሎች ክፍለ አህጉራት ጋር ሊኖራት የሚገባው ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሚጠበቀው ከፍታ አለመጠናከሩ ከፊት ለፊት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ መሪዎቹ እንደተግባቡበት ተገልጿል። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና በቀጣናው የተረጋጋ ሠላም ለመገንባት የተደረሰበት ውጤትም በመልካም ተሞክሮነት ቀርቧል። በተመሳሳይ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በመቃኘት ትርጉም ያለው አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር እንደሚተጉ መሪዎቹ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም