የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለችግር መዳረጉ ተገለጸ

343
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከግል ሞባይል ስልካቸው ጀምሮ እስከ ለበሱት ጫማና ልብስ ድረስ ለሽያጭ እንዲያቀርቡ እያደረገ ያለ ችግር መሆኑ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ በሀገሪቷ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ እየመከረ ነው። በዚህ መድረክ ላይ የመነሻ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ አለሙ ሰይድ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር እውቅና ተሰጥቶት የስፖርት ውርርድ በሚል እየተካሄደ ያለው ጨዋታ በተማሪዎች፣ በሰራተኞች፣ በባለትዳሮችና በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ላይም ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው ብለዋል። ከነዚህ ችግሮች መካከል እንደ አብነት ያነሱት ቤቲንግ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽእኖ ነው። እንደእሳቸው ገለጻ ተማሪዎች ለቤቲንግ ውርርድ ሲሉ የግል ሞባይላቸውን ይሸጣሉ፤ በእሱ ከከሰሩ ደግሞ  ጫማና ልብስ እስከ መሸጥ ድረስ ይወራረዳሉ ብለዋል። አጠቃላይ እንደ ሀገርም በኢኮኖሚ ላይ ወጣቶች በአቋራጭ መክበር እንዲያስቡ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንስ ተግባር መሆኑን ነው ያስረዱት። በስነልቦና ረገድም ለጭንቀት፣ ለድብርት ብሎም እራስን እስከማጥፋት የሚዳርግ ችግር የያስከትል በመሆኑም የሚመለከተው አካል በጊዜ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም