ለበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራ ሕዝቡ ድርሻውን ይወጣ፤ መንግስትም የበኩሉን ያደርጋል --- ግብርና ሚኒስቴር

65
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 (ኢዜአ) እየተባባሰ የመጣውን የአካባቢ መራቆት ለመግታት ሕብረተሰቡ የድርሻውን ይወጣ ያለው የግብርና ሚኒስቴር መንግስትም የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቋል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ትናንት በአርሲ ዞን ሔጦሳ ወረዳ የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ አስጀምረዋል። የተፋሰስ ልማት ስራው የተጀመረበት ሔጦሳ ወረዳ ጉሪ ዳቡላ ቀበሌ ከፍተኛ የአካባቢ መራቆት በማጋጠሙ የስድስት ሺህ አርሶ አደሮች ሕይወት ላይ አደጋ ተጋርጧል ተብሏል። በዚህ ሳቢያም ቀበሌው በክልሉ በስፋት ለሚካሄደው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ማስጀመሪያነት ተመርጧል። ዶክተር ካባ በልማት ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ለተገኙ አርሶ አደሮች ባስተላለፉት መልዕክት የአካባቢ መራቆትን ለመግታት መንግስት ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተፋሰስ ልማት ስራ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውንም አንስተዋል። በአካባቢው እያንዣበበ ያለው አደጋ ከባድ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ካባ "ይህ ተግባር የበለጠ ውጤት ያመጣ ዘንድ ሕዝቡ በአግባቡ ድርሻውን መወጣት አለበት" ነው ያሉት። ይህ ሲሆን ደግሞ መንግስትም የራሱን የስራ ድርሻ ስለሚወጣ፤ የጋራ ጥረቱ የአካባቢና የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራውን ያጠናክረዋል ብለዋል። በእስካሁን ሂደት የዘንድሮውን ሳይጨምር በመላ አገሪቷ ዘጠኝ ሚሊዮ ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ መሰራቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያወሱት። የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪም ሕዝቡ የአካባቢ ጥበቃ ሲባል ውኃን፣ አፈርንና ደንን መጠበቅ ማለት መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ይላሉ። እነዚህ የሰው ልጆች የመኖርና የሕልውና መሠረቶች ስለሆኑ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ በዚሁ ውስጥ መመለስ ይቻላልም ብለዋል። አሳሳቢ በሆነ መልኩ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን ተከትሎ የእርሻ መሬቶች በጎርፍ እየተወሰዱና እየተቦረቦሩ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ከወዲሁ ለመግታት በኦሮሚያ ክልል ከ6 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የሔጦሳ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ መሀመድ አብዶ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማት ስራው በተጀመረበት ቀበሌ ከሚገኝ ተራራ ላይ የሚወርድ ውኃ አስፋልት መንገድ ጭምር እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል። ከተራራ ላይ የሚፈሰው ውኃ ከእርሻ ማሳ ላይ አፈር በመጥረግ ወደ ዝዋይ ሐይቅና አዋሽ ወንዝ እየገባ መሆኑንም እንዲሁ። በመሬት መራቆት ምክንያት በክረምት ወራት የሚከሰተው ጎርፍ ቦሮቦር እየፈጠረ ሕዝቡን አቆራርጧል፤ መጓጓዣም ላይ ችግር ፈጥሯል ነው ያሉት። የቀበሌው ነዋሪዎች ሁኔታው እጅግ እያሳሰባቸው እንደሆነና የተፋሰስ ልማት ስራው መፍትሔ እስከሆነ ድረስ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በ23 የወረዳው አካባቢዎች በሕዝብ ንቅናቄ የተፋሰስ ልማት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም