የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ረቂቅ አዋጅ በክልሎች መካከል የበለጠ ግልጽነትና ፍትሐዊነት የሚያሰፍን ነው ተባለ

99
አዲስ አበባ  ጥር  13/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን እየረቀቀ ያለው አዋጅ በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያሰፈን መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ። ረቂቅ አዋጁ በውይይት እንዲዳብር የህግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። በዚህ መሰረት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ከክልል ተወካዮች፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከህግ ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ምክክር አድርጓል። በወይይት ወቅትም እስካሁን ያለው የክልሎችና ድጎማና የጋራ ገቢ ክፍፍል ሥርዓት ሳይበጅለት ወጥ አሠራር ሳይኖረው በፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ቀመር መሰረት መከናወኑ አድሎዓዊና ፍትሐዊነት የጎደለው አሠራር እንዲኖር አድርጓል ብለዋል። ይሁንና የአዋጁ መውጣት ቢዘገይም አስፈላጊነቱ ግን አጠያያቂ እንዳልሆነ በተወያዮቹ ተገልጿል። በተለይም በልማት ወደኋላ የቀሩ፣ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውና በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ያላቸው ክልሎች በዚሁ አሠራር ተጠቃሚ እንዳልነበሩም እንዲሁ። በረቂቅ አዋጁ ላይ የጋራ ገቢ ክፍፍል አዲስ አበባንና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ለምን አላካተተም?፣ ከጋራ ገቢ ሀብቶች ተብሎ በህገ መንግስቱ ከተጠቀሰው ውጪ ያሉ ሀብቶች በክፍፍሉ ወቅት እንዴት ይታያሉ? እንዲሁም የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ጨምሮ አዋጁ ሊያካትት ይገባል በሚል አስተያየቶችም ተነስተዋል። እስካሁን የፌዴራል መንግሥት የሚመድበውን የድጎማ በጀት ለክልሎች የሚደለድልበትም ሆነ የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት የአሠራር ሥርዓት ወጥነትና ቅንጅት የጎደለው ነበር። በመሆኑም ክልሎች በክፍፍሉ ሚዛናዊነትና ውጤታማነት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋሉ የመጡ ክፍተቶችን ለመቅረፍ መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ገቢራዊ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ አዲሱን ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት ምክንያት መሆኑን የፌዴሬሽን ፎረም ከፍተኛ ማኔጀር አቶ ያዕቆብ በቀለ ተናግረዋል። በተጨማሪም የክፍፍሉ ሒደት የበለጠ ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሕግ ማዕቀፉ እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። የድጎማ በጀት ክፍፍል የክልሎች የወጪ ፍላጎትና እምቅ የገቢ አቅምን፣ ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት እንዲሁም ክልላዊ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችንም ለማጥበብ ነው ብለዋል። በልማት ወደኋላ የቀሩ ክልሎችን መደገፍ፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑም ተናግረዋል። ረቂቅ አዋጁን ለማሻሻል የተለያዩ ምክክረ ሀሳቦች የተደረጉበትና ግብዓት የተወሰደ መሆኑን ገልጸው መሻሻሎች እንደሚደረግበት ገልጸዋል። የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን በተመለከተም በህገ-መንግስቱ የጋራ የገቢ እንዲካፈሉ አልተቀመጠም ይሁንና በቻርተሩ ህግ መሰረት ድጎማ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል። የጋራ ገቢ ክፍፍልን አስመልክቶም በህገ-መንግስቱ ከተቀመጡት ውጪ አዳዲስ ሀብቶች ሲገኙ በተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል። ከፌዴራል ድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ጋር የተያያዙ ተግባራትና ኃላፊነቶቹን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያግዘው ራሱን የቻለ ህጋዊ ሰውነት ያለውና ተጠሪነቱም ለምክር ቤቱ የሆነ በዋናና በምክትል ኮሚሽነርነት የሚመራ ኮሚሽን ይቋቋማል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም