በመጪዎቹ አስር ቀናት በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማው የአየር ሁኔታ ይቀጥላል

58
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 13/2012 በቀጣዮቹ አስር ቀናት በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች እየታየ ያለው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው እንዳስታወቀው በእነዚህ ቀናት አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ይኖራቸዋል። ይህም ለመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ድህረ ምርት ስብሰባ ጠቃሚ በመሆኑ አርሶ አደሩ የድህረ ምርት ስብሰባውን እንዲያጠናክር አሳስቧል። በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የደመና ሽፋን መጨመርና አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖርም አርሶ አደሩ ምርቱን በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል ብሏል። አነስተኛ የዝናብ መጠን ከሚያገኙ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ኦሮሚያ ጅማ፣ ኢሉባቡር፣ ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢና የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖችን ጠቅሷል ኤጀንሲው። በአንፃሩ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በአንዳንድ ደጋማ ስፍራዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው የተነበየው። የተቀሩት የአገሪቷ አካባቢዎች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩም አመልክቷል። የሚጠበቀው የበጋው ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ ለቋሚ ተክሎችም ሆነ ለግጦሽ ሳርና መጠጥ ውሃ አቅርቦት አሉታዊ ጎን እንደሚኖረው ጠቁሟል። በአብዛኞቹ ተፋሰሶች ላይ ደመናማና ፀሐያማ የአየር ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን ጥቂት ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ከነዚህም መካከል በታችኛው ምስራቃዊ አባይና አዋሽ አዋሳኝ፣ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ የመካከለኛው ኦሞ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ይገኙበታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም