በጎንደር የጥምቀት በዓል አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል...የጎንደር ከተማ አስተዳደር

61
ጎንደር ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) በጎንደር ባህረ-ጥምቀት ላይ በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ወገኖችና ቤተሰቦች ድጋፍ የሚያሰባስብ ኮሚቴ መዋቀሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ። የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የማማውን ጥራትና የግንባታ ሁኔታ ሲቆጣጠሩ ከነበሩ የመምሪያው መሐንዲሶች ጋር  ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ እንዳመለከቱት ሰባት አባላትን ይዞ ሥራ የጀመረው ኮሚቴ በአደጋው ለቆሰሉ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚያሰባስብ  ነው። በአስተዳደሩ የሰላምና የሕዝብ ደህንነት መምሪያ ሰብሳቢነት የሚመራው ኮሚቴው ፖሊስ፣ ፍትህ፣ ክርስቲያን ኅብረት ጽህፈት ቤት፣ ሰላምና ልማት ሸንጎ፣ የወጣቶች ማህበርና ህንፃ ሹምን ያካተተ ነው። "በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምና ላይ ላሉ ተጎጂዎች ድጋፍ እያደረግን ነው" ያሉት ኃላፊው፣በቀጣይም አስተዳደሩ ከኮሚቴው ጋር በመቀናጀት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ኮሚቴው ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ የጉዳቱን ሁኔታና መጠን ለማጣራት ኃላፊነት እንደተሰጠውም አቶ አስቻለው አስረድተዋል። በመምሪያው የቅርስ ጥገና ባለሙያ አቶ ማሞ ጌታሁን እንዳሉት አደጋው የደረሰው  ከማማው የጥራት ጉድለት ሳይሆን፣ መሸከም ከሚችለው መጠን በላይ በመያዙ ነው። ማማው የሚይዘው ከ460 ያልበለጡ ሰዎችን ቢሆንም፤ከዚያ በእጥፍ የሚበልጡ ሰዎች ማማው ላይ በመውጣታቸው አደጋው እንደተከሰተ ገልጸዋል። በቀጣይም በብረት ለሚሰራው ማማ ከሚያስፈልገው ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የአውሮፓ ኅብረት ሁለት ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መገባቱንም አቶ ማሞ ተናግረዋል፡፡ በአደጋው 10 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በ245 ግለሰቦች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ  ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም