ኬንያውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተዘርግተዋል

60
ጥር 13 /2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኬንያውያ ባለሀብቶች ኃብታቸውንና ዕውቀታቸውን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ተቋማዊ አሰራሮችን መዘርጋቷን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ። የኢትዮጵያና ኬንያ አጎራባች ክልሎች የንግድ ባዛር በኬንያ ሞያሌ ከተማ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሄዳል። በኬንያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኬንያ የወጪ ንግድ ፕሮሞሽንና ብራንዲንግ ኤጀንሲ ስራ ኃላፊዎች  በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው ከአምባሳደር መለስ ዓለም ጋር ተወያይተዋል። በናይሮቢ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ መጠን ለማሳደግ መንግስት በልዩ ትረኩት እንደሚሰራ አስረድተዋል። አምባሳደር መለስ ''ኢትዮጵያ ኬንያውያን ባለሀብቶች ኃብታቸውንና ዕውቀታቸውን ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እና ተቋማዊ አሰራሮችን ዘርግታለች'' ብለዋል። ኬንያውያን ባለሀብቶች የተዘረጉትን ምቹ አጋጣሚዎች በመጠቀም በግብርና ማቀነባበር፣ በጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የኬንያ የወጪ ንግድ ፕሮሞሽንና ብራንዲንግ ኤጀንሲ ኃላፊ ኦስቲን ማቼሶ በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ንግድ መጠን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በባዛሩ ላይም የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለኬንያ ገበያ እንዲያስተዋውቁና ከኬንያ ነጋዴዎች ጋር የጠበቀ ትብብር እንዲኖራቸው ለማድረግ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቀዋል። የኬንያ ኢንቨስተሮችን ከኢትዮጵያ ገበያ ጋር ለማቆራኘትና የንግድ ግንኙነቱን ለማሳደግም ከኤምባሲው ጋር ተባብረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም