ተቋማቱ የሰው ኃይል ልማትን በጥራትና በብቃት የሚያወጡበት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ጀመረ

86
አዳማ  ጥር 13 /2012 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል ልማትን በጥራትና በብቃት የሚያፈሩበት ፎኖተ ካርታ ወደ ትግበራ መግባቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ። ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለኢትዮጵየ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ፍኖተ ካርታው ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ የሰው ኃይል ለማልማትና ለማሰልጠን ያስችላቸዋል። ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር በአገሪቷ በሚገኙ 50 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችና በ1ሺህ 620 የግልና የመንግሥት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት  ለአንድ ዓመት  ጥናት መደረጉን አመልክተዋል። በዚህም ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉት የትምህርት ሴክተር ምሁራን፣የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። የፍኖተ ካርታው አንዱ አካል የሆነው ተቋማቱን በተልዕኮ፣በጥናትና ምርምር፣ በልህቀት ማዕከል እንዲደራጁ እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ለዚህም ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል። በያዝነው የትምህርት ዘመን ተቋማቱን የተቀላቀሉ ከ140ሺህ በላይ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚቆዩ የጋራ ኮርሶች በመውሰድ ላይ ናቸው ብለዋል። በተመሳሳይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና አሰልጣኞች ሙሉ በሙሉ ፕሮፌሽናል እንዲሆኑ የስልጠና ማኑዋል ተዘጋጅቶ በ650 ኮሌጆች በዲፕሎማ ደረጃ የነበሩ መምህራን የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲይዙ ተደርጓል ብለዋል። በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን ሥርዓተ ትምህርት ለመለወጥና  ጥራትና ብቃት ባለው የሰው ኃይልና ቁሳቁስ አደራጅቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ እየተሰራ  መሆኑን ፕሮፌሰር ካሱ አመልክተዋል። የሙያና ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን ወደ ዩኒቨርሲቲ በማሳደግ ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በቀጥታ የሚቀበሉበት ሁኔታ ለመፍጠርና  ለዚህም ከኢንዱስትሪው ጋር የተቆራኘ ሥርዓተ ትምህርት እየተቀረፀ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህም የአገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ብቁና ጥራት ያላቸው የመካክለኛ ደረጃ ምሁራንን በብዛት በማፍራት ግብ መቀመጡን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድጸዋል። የሚኒስቴሩ የእቅድና የሀብት ማፈላለግ ዳዳይሬክተር አቶ አዱኛ በቀለ ፍኖተ ካርታውን ውጤታማ ለማድረግ 11 ስትራቴጅክ ግቦችና የተለያዩ ዝርዝር መስኮችን የያዙ 90 የሚሆኑ የማስፈፀሚያ ስልቶች ተቀርፀው ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ፍኖተ ካርታው አገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሰው ኃይልን በጥራትና በብዛት ለማፍራት እንደሚያስችል እምነቱን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም