በኢትዮጵያ 560 የሽርክና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ነው

103
አዲስ አበባ ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ 560 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሃብቶች ሽርክና እየተተገበሩ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መኮንን ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት 560 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶች እ.አ.አ ከ2014-2019 በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ እየሰሩ ነው። ይህም የአገሪቷን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ከማረጋገጥ ባለፈ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ያግዛል፤ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትም ዕድል ይፈጥራል። የሽርክና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በቅድመ ትግበራ፣ በትግበራና በምርትና አገልግሎት መስጠት ሂደት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ መኮንን 182ቱ ምርትና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል። ሌሎች 114 ኢንቨስትመንቶች በትግበራ ሂደት ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 264 በቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ ናቸው። ቻይናዊያን ባለሃብቶች ከኢትዮጵያዊያን ጋር በሽርክና በመስራት ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ የአሜሪካ፣ የሕንድ፣ የጃፓን፣ የካናዳ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሱዳንና የስፔን ባለሃብቶችም ይጠቀሳሉ። ባለሃብቶቹ ከሚሳተፉባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የማምረቻ ኢንዱስትሪ 350 ፕሮጀክቶችን በመያዝ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። ግብርና፣ ቤቶች ግንባታና ማሽነሪ፣ ኮንስትራክሽን፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ቱር ኦፕሬሽንና ትራንስፖርት፣ ጤና፣ ትምህርትና ሌሎችም በሽርክና የሚሰሩባቸው ዘርፎች እንደሆኑ አቶ መኮንን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም