የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲታይ ተወሰነ

59
አዲስ አበባ ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲፈተሽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ። ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል። የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓትን ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለግንኙነቱ ግልጽና ሕጋዊ ሥርዓት ለማበጀት ያለመ ነው። የክልል መንግሥታት ያሏቸውን ሥልጣንና ተግባራት በማይጋፋ መልኩ እንዲቀራረቡና የጋራ ዕቅድ ነድፈው እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል ተብሏል። በየእርከኑ በመግሥታትና አቻ ተቋማት መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተገልጿል። በዚህም መሰረት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሠላም እሴቶች ግንባታ ጥናት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ ረቂቁ በአፋጣኝ እንዲፀድቅ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ ተወያዮቹ በረቂቁ ላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮች እንደ ክልል መጠቀሳቸው አግባብ እንዳልሆነ አንስተዋል። ይህም ረቂቁ 'ለክልል መንግሥታት የጎንዮሽ ግንኙነት' እና 'የክልልና የፌዴራል መንግሥት የተዋረድ ግንኙነትን እንደሚመለከት' ከሚለው ጋር ይጣረሳል ብለዋል። በሌላ በኩል ረቂቁ ክልልና የፌዴራል መንግሥትን በእኩል አተያይ የማቅረብ አዝማሚያውም ግልጽነት እንደሚጎድለው ተጠቁሟል። ተያይዞም በረቂቁ ላይ ደንብ የሚያወጣው አካል ተለይቶ አልተቀመጠም በመሆኑን ረቂቁ ሙሉ ነው ለማለት ያስቸግራል ሲሉ ተወያዮቹ ገልጸዋል። ረቂቁ ሕገ-መንግሥቱ ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ይፅደቅ የሚል ሃሳብም ተነስቶ በዚህም ላይ በጉባዔተኛው መቋጫ አልተገኘለትም። በአንጻሩ ረቂቅ ሕጉ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ ጋር ሲነጻጸር ይህ አይነቱን ሕግ በማርቀቅ ኢትዮጵያ መዘግየቷ ተጠቁሞ በአፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተብሏል። በረቂቁ መንግሥታት በሚመሰርቷቸው መድረኮች ውሳኔዎች በሶስት አራተኛ ድምፅ እንዲፀድቅ በሚለው ላይም፤ በማይገኙ የመድረኩ አባላት ላይ ተፈጻሚነትን በተመለከተ ግልጽነት ይጎድለዋል ተብሏል። ረቂቁ አስገዳጅ ነው ወይስ በስምምነት በሚለውም ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል። እነዚህን የግልጽነት ጥያቄዎች የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው ረቂቁ በደንብ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በማሰብ ዳግም እንዲታይ ወስኗል። የቴክኒክ ኮሚቴውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተነሱትን የግልፀኝነት ጥያቄዎች በተመለከተ አሻሻሎ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያመጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም