ብሔራዊ ሎተሪ ከስፖርት ውርርድ /ቤቲንግ/ 22 ሚሊዮን ብር ገቢ አገኘሁ አለ

314

 አዲስ አበባ ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ)  የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ባለፉት አምስት ወራት ከስፖርት ውርርድ /ቤቲንግ/ 22 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቻለሁ አለ።

በሌላ በኩል በስፖርት ስም የሚካሄደው ውርርድ ህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እየከተተ በመሆኑ ሊታገድ ይገባል ሲሉ ግለሰቦችና አንድ የስነ ልቦና ባለሙያ ገልጸዋል። የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ይህ የስፖርት ውርርድ በህገወጥ መልኩ ሲሰራበት እንደነበር ይናገራሉ።

አስተዳደሩ ይህን ህገ-ወጥ ስራ ህጋዊ መስመር በማስያዝ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለአጫዋች ድርጅቶች ፍቃድ በመስጠት እየሰሩበት ነው።

በአሁኑ ወቅት ከህብረተሰቡ ቅሬታዎች እየቀረቡ በመሆኑ ለጊዜው ፍቃድ የመስጠቱ ስራ መቆሙን የገለጹት ዳይሬክተሩ መስተካከል ያለባቸው አሰራሮችና መመሪያዎች ተስተካክለው ፍቃድ መስጠቱ ይቀጥላል ብለዋል።

የስፖርት ውርርድ በዓለም ላይ ያለ ነው ኢትዮጵያም ከዓለም የምትወጣ አገር አይደለችም ነው ያሉት።

አቶ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ሎተሪ ባለፉት አምስት ወራት ከአጫዋች ድርጅቶች በኮሚሽን 22 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷልም ብለዋል።

በሌላ በኩል የስፖርት ውርርድ ፍቃድ በጊዜያዊነት ሳይሆን አጠቃላይ መከልከል ያለበት ተግባር ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ግለሰቦችና የስነ ልቦና ባለሙያ ገልጸዋል።

በርካታ ወጣቶች የስፖርት ውርርዱ ተጠቂ እየሆኑ በመሆኑ መንግስት እርምጃ ሊወስድ ይገባል የሚሉት አሚር ከድር ና ገዛኢ አግዛ ።

ወጣቶች ሰርተው ሳይሆን በአቋራጭ መበልፀግን በማሰብ ስራ የሚጠላ ትውልድ የሚፈጥር ነው፤ ህብረተሰቡንም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ይዳርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በቀጣይ የአገርን ኢኮኖሚም ሊጎዳ የሚችል ተግባር ነው ይላሉ።

የስነ-ልቦና ባለሙያው ዕጩ ዶክተር ዳዊት ቶማስ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች አንድ አገር ከወጣቱ ማግኘት ያለበትን ጊዜና ጉልበት እንዳያገኝ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ያደርሳል ይላሉ።

ተቋም ሲመሰረት ለህዝብ የሚጠቅም እንጂ ህዝብን የሚጎዳ ከሆነ መንግስታዊም ሆነ የግል ድርጅት አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ።

የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች አደጋ ላይ የሚጥል ተቋም እንዲኖር ፍቃድ የሚሰጠው አካል ራሱን መፈተሽና ማየት ይጠይቃልም ብለዋል።

በዚህ ውርርድ የሚሳተፉ ሰዎች ከአጫዋች ድርጅት ማሸነፍ ቢችሉ እንኳ ገንዘቡን ቀጣይ ህይወታቸውን ለሚያመሰቃቅሉና ወንጀል ነክ ለሆኑ ጉዳዮች የመጠቀም ዕድላቸውም ሰፊ ነው ይላሉ።

ቤቲንግ በብሄራዊ ሎተሪ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶት የስፖርት ውርርድ በሚል ስያሜ በመላ አገሪቷ እየተስፋፋ ይገኛል።

አንዳንድ አገራት በዚህ የስፖርት ውርርድ ላይ እገዳ እያደረጉ ነው።

ዩጋንዳና ኬኒያ ባለፈው ዓመት ውርርዱ እያስከተለባቸው በመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሳቢያ እገዳ ከጣሉ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ከ30 በላይ ህጋዊ ፍቃድ የወሰዱ የስፖርት ውርርድ /ቤቲንግ/ አጫዋች ድርጅቶች  መኖራቸውን ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም